




በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 5,000 ሊትር ናፍጣ በቁጥጥር ስር ማድረጉን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ።
በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር ለመግታት የሚደረገው የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማረ ቶቲ እንደገለጹት፤ ከፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመቆጣጠር የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
በተለይም በምሽት ጭምር የሚንቀሳቀስ የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ኦፕሬሽን በመጀመሩ፣ ተከታታይነት ያለው ህገ-ወጥ ናፍጣና ሌሎች የነዳጅ ውጤቶች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ ማደያዎች የሚያስመጡት ነዳጅ በአግባቡ ለህዝብ እንዲሰራጭ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም የችግሩ ምንጭ ሙሉ በሙሉ አለመድረቁንና በተደራጀ መልኩ በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ምናሉ ታደሰ ስለ ኦፕሬሽኑ ዝርዝር መረጃ ሲሰጡ እንደገለጹት የተያዘው ነዳጅ 5,000 ሊትር ናፍጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ናፍጣው በአይሱዙ ተሽከርካሪ ተጭኖ በምሽት 4:00 ሰዓት አካባቢ በፖሊስ ድንገተኛ ፍተሻ ተይዟል።
ነዳጁን ሲያጓጉዙ የነበሩ አሽከርካሪውና ረዳቱ ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል።
ኮማንደር ምናሉ አክለው እንደገለጹት፣ በትናንትናው ዕለትም ከ470 ሊትር በላይ ቤንዚንና ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሰዋል።
ከቀጥታ የነዳጅ መያዝ ኦፕሬሽኑ ጎን ለጎን፣ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ህገ-ወጥ አሰራሮችን ለመቀነስ ተጨማሪ የነዳጅ ታንከር (ሳልቫቲ) ከተገቢው በላይ ነዳጅ ለመቅዳትና ለመነገድ ተብሎ በተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠሙ ተጨማሪ የነዳጅ ታንከሮች (ሳልቫቲዎች) እንዲወርዱ ተደርጓል፣ ነዳጅን በየቤታቸው ደብቀው በሚሸጡ ግለሰቦች ላይ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
የማደያዎች ቁጥጥርን በተመለከተ በነዳጅ ማደያዎች ላይም ተገቢው ማጣራት እየተደረገ ሲሆን፣ ግድፈት በተገኘባቸው ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።
በመጨረሻም፣ ህብረተሰቡ ህገ-ወጥነትን በመከላከል ረገድ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ከፖሊስ ጎን እንዲቆም የከተማው የጸጥታ አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል ሲል የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
