በበጀት ዓመቱ ከ629 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የአርብቶአደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርብቶአደርና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ፥ ምዕራፍ ሁለት የቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የእስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በቆላማ አከባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ማጠቃለያ እና የምዕራፍ ሁለት ትውውቅ ለባለድርሻ አካላት በትናንትናው ዕለት መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው እለት በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ላይ የእስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአርብቶና ከፊል አርብቶአደር ኑሮ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲጠናከር የክልሉ የአርብቶአደርና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኩ በመክፈቻ ንግግራቸው ጠይቀዋል።

በምዕራፍ አንድ የፕሮጀክቱ ትግበራ መልካም ውጤት መመዝገቡን የገለጹት አቶ መቱ በምዕራፍ ሁለት መልካም ተሞክሮዎችን በማከል በተሻለ መልኩ መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፕሮጀክቱ ዓላማ በክልሉ የሚገኙ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ኑሮ ማሻሻልና ከአየር ንብረትን ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም አቅምን ማሳደግ መኾኑ ነው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ ያስረዱት።

የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ለእስሪንግ ኮሚቴ ያቀረቡት አቶ ደረጀ፥ ፕሮጀክቱ በካፋ ዞን፥ የጎባ ወረዳ፤ በምዕራብ ኦሞ ዞን፥ መኤኒት ጎልድያ፣ መኤኒት ሻሻ፣ ሱሪ እና ማጂ ወረዳዎች በ99 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ125ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ አስረድተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና አንድ ተጨማሪ አዲስ ፕሮጀክት በአርብቶና ከፊል አርብቶአደር አከባቢ ለማከናወን 629 ሚሊዮን 275ሺ ብር በጀት መያዙን ነው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ የገለጹት።

ፕሮጀክቱ በዋናነት፥ በአርብቶአደር አከባቢ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም የሚሰሩ የአደጋ ስጋት አስተዳደር፣ የተቀናጀ የግጦሽ መሬት አስተዳደር እና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የኑሮ ማሻሻያ ተግባራት ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ነው አቶ ደረጀ ያስታወቁት።

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የውሃ ግንባታና የመስመር ዝርጋታ፣ የመንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ ተሰጥተው ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በቀረበው የ2018 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱ ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጎ በእስትሪንግ ኮሚቴ እንደሚፀድቅ ከወጣው መርሀግብር መረዳት ተችሏል።

በመድረኩ የእስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *