ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መከበር ሁሉም በተሰማራበት የሙያ መስክ ለአገሩ የሚጠበቅበትን ማበርከት አለበት

Spread the love

ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መከበር ሁሉም በተሰማራበት የሙያ መስክ ለአገሩ የሚጠበቅበትን ማበርከት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

በሉዓላዊነት የተሰየመው ጳጉሜ-3 “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ኃሳብ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር የተከፈለን ዋጋ ክብር በመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ተክብሮ ውሏል።

በሳይንስ ሙዚየም የተሰናዳው ዝግጅትም የፓናል ውይይትን ጨምሮ ለአገር ነፃነት የተከፈለን ውድ ዋጋ የሚያሳይ የአውደ-ርዕይ ዝግጅትና በሕፃናት የሉዓላዊነት የመዝሙር ሥነ-ሥርዓት ተክብሯል።

በዚሁ ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ በሉዓላዊነታችን ለማንደራደር ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የሉዓላዊነት ቀንን ማክበር የላቀ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ክብር ታፍሮ ተጠብቆ እንዲቀጥል ውድ ሕይወታቸውን ያለስስት ለሰጡ፣ ደማቸውን ላፈሰሱና አካላቸውን ላጎደሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ምስጋናቸውን ችረዋል።

ሉዓላዊነት በደምም በላብም የሚጠበቅ እሴት ነው ያሉት አቶ ተመስገን የአገር ነፃነት፣ ዳር ድንበርና የወገን ክብርን መጠበቅ የሚቻለውም በደም መስዋትነት ነው ብለዋል።

የአገርን ሁለንተናዊ የፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የበጀት ሉዓላዊነትም በደምና በላብ አጽንቶ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ነፃነት ከልመና፣ ጥንታዊነት ከኋላቀርነት፣ ክብር ከተረጂነት ጋር አብረው የሚሄዱ ጉዳዮች ባለመሆናቸው ይህ ትውልድ ለተሟላ ሉዓላዊነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት መገለጫ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየ ነፃነትና የማይደፈር አገራዊ ሉዓላዊነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የተጎናጸፈችው ታሪካዊ ጸጋም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ጥቁር ሕዝቦች ጭምር ተምሳሌት የተሞላበት የኩራት ምንጭ ሆኖ መዝለቁን ገልጸዋል።

ኢትዮጵዊያን በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድልም አንዱና ዋነኛው መሰረታዊ የሉዓላዊነታችን መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓድዋን የድል መንፈስ በተሰማራንበት የሙያ መስክ በመድገም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብም የአሁኑ ትውልድ ተልዕኮ ነው ብለዋል።

የብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ማስከበር አንዱ የአገርን የተሟላ ነፃነት ማስከበሪያ አምድ ነው ብለዋል።

ለዚህም ሰብዓዊነትን ለመመገብም በምግብ ዋስትናና በምግብ ሉዓላዊነት ማዕቀፍ የተሟላ ሉዓላዊነትን ለመጎናጸፍ የግብርና ምርታማነት ስኬትን ማስቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ካርታ መለዮ ለባሹ በደምና አጥንቱ የሳለው ነው ብለዋል።

ለዚህም የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነው መላዮ ለባሹም እራሱን ችሎ የአገሩን ሉዓላዊነት በመጠበቅ ነፃነትን የሚያስከብር ሁሉንም ህዝቦች ያለአንዳች ልዩነት አክብሮ የሚያገለግል ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በደምና ላቡ የሚከፍለው መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር መሆኑን መዘንጋት የለበትም ያሉት ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ፤ በቀጣይም ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር አጽንቶ ይቀጥላል ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬቶችን በማስቀጠል ከልመናና ምጽዋት ማስወጣት የሚያስችል ትውልድና አገር ገንብቶ ማስተላለፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርኃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጳጉሜ-3 “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት የተከበረ ሲሆን፤ ከቀኑ 6፡00 ላይም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ውድ ዋጋ ለከፈሉ ጀግኖች ክብር በመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *