


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ2016 በጀት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት አመት ጠቋሚ ዕቅድ ዙሪያ ከዞን፣ወረዳ የፖሊስ አመራሮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ እየመከረ ይገኛል።
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፖሊሲ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስበ ሸዋኖ በ2016 በጀት ዓመት ተቋማዊ የመፈጸም አቅምን በማሳደግና አሰራሮችን በማጎልበት በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
ማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ግንዛቤ ከማሳደግ በተጓዳኝ የማህበረሰብ ፖትሮል የማደራጀት እንዲሁም አማካሪ ምክር ቤት በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች በማዋቀር ወደ ተግባር ማስገባት መቻሉ ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር እና የህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በብቃት በመቆጣጠር 200 የጦር መሳሪያ እንዲሁም ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግሥት ካዘን ገቢ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የመንገድ የትራፊክ ቁጥር እና የማህበረሰብ ግንዛቤ በማሳደግ የትራፊክ አደጋን ከለፈው ዓመት በንጽጽር 24 ከመቶ እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉን የሚገልጹት ኮሚሽነሩ ይሁን እንጅ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት በዋዛ እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ አደጋ የመከላከሉ ስራ ቀጣይ ትኩረት የሚሻ የቤት ስራ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
በተለይ በዘርፉ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቋረጡ መዝገቦች መብዛት፣የምርመራ ጥራትና የማጣራት ምጣኔ፣ የተከሳሽና ማስረጃ አቀራረብ፣የኤግዚቢቶች አያያዝ፣ መርማሪ ፖሊስና የአቃቤ ህግ ቅንጅታዊ ሥራ፣ በየማረፊያ ቤቶች የተያዙ ሰዎች አያያዝና ያለአግባብ የማሰርና የመፍታት ሁኔታ፣ የብርበራና መያዣ ትዕዛዝ ሚስጢራዊነትን ከመጠበቅ አኳያ፣ መዝገብን እንደኑሮ መደጎሚያ የመጠቀም ሁኔታ በየቦታው እየተስተዋለ በመሆኑ አጽንኦት ልሰጠው ይገባል ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ለ211 የፖሊስ አባላት የተለያየ የአቅም ግንባታ የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልጠና በሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር መሰጠቱን በማንሳት ይህም የፖሊሲን የወንጀል መከላከልና የመፈጸም እንዲሁም የምርምር አቅም የሚጨምር መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።
ፖሊሲ የህዝብ ሠላምና ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮ በብቃት በመወጣቱ በክልሉ ሁሉም አከባቢ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል ያሉት የክልሉ የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ መጨመሩን ገልጸዋል።
በመደበኛ የወንጀል መከላከልና ምርመራ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በተያዘው በጀት ዓመት ከፍ ያለ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ አንድነት በ2016 በጀት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በተያዘው በጀት በሁሉም መስክ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ክልሉ ከምሥረታው በፊት ከሚታወቅበት የሠላም ሁኔታ አሁን ላይ ተሻሽሎ በሀገር ደረጃ የሠላም ተምሳሌት ሆኗል ያሉት አቶ አንድነት በዚህም ፖሊሳዊ ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለጽ የመጣውን ሠላም ማስቀጠል፣ ወንጀል መከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በጉባኤው የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም በክልሉ ፖሊሲ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቁ በድሩ እየቀረበ የሚገኝ ስሆን በቀጣይ የ2017 ጠቋሚ እቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድም ተገልጿል።
በመድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማርያምን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችና የሁሉም መዋቅር የፖሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
