በክልሉ የሚገኙ ህብረት ስራ ማህበራት ተወዳዳሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አሰፈላጊው ድጋፍ ይደርጋል፦ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ <<የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም የህብረት ስራ ማህበራት ለኢትዮጵያ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ የህብረት ስራ ማህበራት ድንበር ተሻጋር፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የማህበራትን አደረጃጀት ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለያዩ ምክንያት እየተዳከመ የመጣው የህብረት ስራ ማህበር በሙሉ አቅም በህግ ማዕቀፍ እና በአደረጃጀት እንደገና በማሻሻል በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ ባለድርሻ አካላት ረፎረሙን መረዳትና ማስረጽ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ማህበራት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በፋይናንስና በአኮኖሚ እንዲበልጽጉ ማህበራት ያለባቸውን ችግሮች ለማረም እና ሪፎርሙ ተግባራዊ እንዲሆን የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ 2050 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት መኖራቸውንና ከዚህም ከ900 በላይ የሚሆኑ በችግር ውስጥ በመሆናቸው ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ማህበራት ለህብረሰተቡ ተመራጭ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

የህብረት ስራ ማህበራት አደረጃጀትና አመራር ከብልሹ አሰራር ነጻ በማድረግ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አንስተዋል።

ክልሉ የግብርና ፤እንስሳት፣ማዕድን ክምችትና የሰፊ አምራች እንዲሁም ሰላሙ የተረጋጋ አከባቢ እንደሆነም የገለጹት የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዱ ሙሀመድ ናቸው።

ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ይህንን ምቹ ሁኔታዎች መጠቀም እንደሚጠበቅባቸውና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ኮሚሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው ህብረት ስራ ማህበራት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የህብረተሰቡ የገበያ ሁኔታ እንዲያረጋጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

በንቅናቄው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ( ዶ/ር ኢ/ር)፤የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮማሽነር አቶ አብዲ ሙመድ ጨምሮ ከክልል እስከ ከተማ አስተዳደር ድረስ ያሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *