በአርብቶአደር ቀጠና ሠላም ለማስፈን በተሰጠው ልዩ ትኩረት አውንታዊ ለውጥ ተመዝግቧል – አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤሮ ወረዳ ሠላምን በማጽናት ልማት ለማስቀጠል ያለመ የአመራር ውይይት በጀባ ከተማ አካሂደዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥ የክልሉ መንግሥት በአርብቶአደር ቀጠና የሚስተለውን የፀጥታ ችግር በመፍታት ልማት ለማረጋገጥ በሰጠው ልዩ ትኩረት አውንታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በዚሁም ለወትሮው በፀጥታ ስጋት ስማቸው በግምባር ቀደምትነት ይነሳ የነበሩ የክልሉ የአርብቶአደር አከባቢዎች አሁን ላይ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኖ ወደ ልማት መግባታቸውን በማንሳት ከእነዚህም አንዱ የቤሮ ወረዳ መኾኑን ጠቁመዋል።

አመራሩ የአከባቢውን ፀጋ በውል በመረዳትና በመለየት ወደ ልማት መቀየር እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ፍቅሬ፥ በቀጠናው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክረው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከአጎራባች አከባቢዎች ጋር ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስር መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ፍቅሬ፣ የብልፅግና ፓርቲ ዕሳቤ የኾኑ እውነተኛ ወንድማማችነትና ህብረብሔራዊ አንድነት በቀጠናው መጠናከር ይገባል ብለዋል።

የማዕድን ሀብት በባህሪው አላቂ በመኾኑ ከዘርፉ የሚመነጨውን ሀብት ወደ ሌሎች ልማት በማሸጋገር በአከባቢው ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።

የአከባቢው የተደመረ የህዝብ አቅሞችን በማቀናጀት በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት የወረዳው አመራሮች፥ የወረዳውን አቅም በጉልህ እየተፈታተነ ያለውን የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በቀጠናው በስፋት ይስተዋሉ ይነበሩ ህገወጥ ተግባራትና የፀጥታ ችግሮች አሁን ላይ በአንጻሩ መቀነሳቸውን የገለጹት አመራሮቹ፥ ይህ ውጤት የተገኘው የክልሉ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት መኾኑን ገልጸዋል።

በአዋሳኝ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችን ለመፍታት ከአቻ መዋቅሮች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች መጠናከር እንዳለባቸው ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ከዚህ ባሻገር የውጥ አቅሞችን የማደራጀት ሥራው በትኩረት እየተሰራ መኾኑን አስረድተዋል።

በአከባቢው የተገኘውን ሠላም በማጽናት ልማት ተደራሽ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ችግሮች ከመፍታት አኳያ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን የክልሉ መንግሥት በእቅድ አካቶ መስራት እንዳለበት አንስተዋል።

በወረዳው የህዝብ የልማት አቋሞችን በተደራጀ መልኩ በማቀናጀት ልማትን ለማምጣት እየተደረገ ያለው አርያነት ያለው ተግባር ለሌሎች የክልሉ አከባቢዎች ተሞክሮ የሚኾን እንደኾነም በመድረኩ ተነስቷል።

በቀጠናው ዘላቂ ሠላም በማስፈን ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማምጣት አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በመግለጽ በመድረኩ ዓላማ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ በስኬት ተጠናቋል።

በውይይት መድረኩ የክልልና የምዕራብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቤሮ ወረዳ እና የጀባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *