ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ለኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ እውቅና የሰጡ ናቸው –
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ለኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ እውቅና የሰጡ ናቸው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የ2016 ዓ.ም ዋና ዋና የመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በቀጣናው ወሳኝ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ብሔራዊ ድል መሆኑን አንስተው፤ ይህም የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል አገር መሆኗን ጠቁመው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች ለኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ታሪክ እውቅና የሰጡ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴም ተገቢውን እውቅና የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ዘርፎች መነቃቃት እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በተጨማሪም የአገሪቱን የገበያ አማራጮችን ያሰፋል፤ የትብብር ማዕቀፎች እንዲጎለብቱ ትልቅ ሚና ይኖራዋልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተቀባይነት በመጠቀም በባለብዙ ወገን መድረኮች ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ጥቅሞች እንድትቆም ዕድል ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል።
