




የኮንታ ዞን ም/ቤት 4ኛ ዙር 4ኛ የስራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 2 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ም/ቤት አፈ- ጉባኤ የተከበሩ አቶ ብርሃኑ አቱሞ ም/ቤቶች በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን የህብረተሰቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት እንዲፋጠን የማድረግ ኃላፊነት በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ባለፉት 6 ወራትም የወጡ ህጎች አፈፃፀማቸውን መከታተል የመገምገምና ግብረ መልስ የመስጠት፣ የዜጎች መብቶችና ነፃነት እንዲከበርና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ፣ የህዝብ አስተያየት መድረክ በማዘጋጀትና አቤቱታና ጥቆማ በመቀበል መፍትሄ እንዲሰጥ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ በጋራ ጥረት በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው የህብረተሰቡን እርካታ ከፍ እያደረጉ ናቸው ያሉት አቶ ብርሃኑ በቀጣይም መሻሻሎች በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መስራት ያሻል ብለዋል።
አክለውም ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የም/ቤቱ አባላት የጎላ ሚናቸውን እንዲወጡና ለምርጫ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉባኤው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የአስፈጻሚ አካላት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የተለያዩ ደንቦች፣ የከፍተኛ ፍ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ ልዩ ልዩ ሹመቶችና ሌሎች አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው እንደሚፀድቁ የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
