




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በተከበሩ ወንድሙ ኩርታ የተመራው የም/ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ቡድን በቦንጋ ከተማ የሚገኘውን የገብረፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታልን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ዓላማ በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ምልከታ በማድረግ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ለተሻለ አገልግሎት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይ ያተኮረ እንደሆነ አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የተሻለና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት የሆኑት በድንገተኛ ክፍልና ቀዶ ጥገና ክፍል የአልጋና ሌሎች የህክምና ቁሳቁስ እጥረት፣ የመድኃኒት እጥረት፣ የደም ኬሚስትሪ ማሽን መበላሸትና ግብዓት አለመሟላት፣ የሲቲ ስካን እና የአጥንት ህክምና ማሽን ያለመኖር እና መሰል ችግሮች የተሻለ ህክምና ለመስጠት አዳጋች መሆናቸውን የድንገተኛ ህክምና ክፍል አስተባባሪና ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር አክሊሉ አየለ ለጎብኚዎቹ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በሆስፒታሉ የታማሚዎች ታርክ በየክፍል ማውጣት፣ የCVC ማሽን መገዛቱና ቁጠባ መኖር ፣ በግዥ ለማይገኙ መድኃኒት ቁጥጥር ስርዓት ማበጀት መቻሉ፣ የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሻሻል በዞኑ መንግስት በጀት ህንፃ እየተገነባ መሆኑ በጥንካሬ የሚወሰዱ ቢሆንም በእናቶችና ህጻናት አከባቢ የመረጃ አያያዝ ስርዓት መስተካከል እንደሚገባ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደ ተግዳሮት የተነሱ ጉዳዮችን ለይቶ በመውሰድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉብኝቱ ተጠናቋል።
በጌታሁን ግርማ
