


በሚዛን አማን ከተማ ስቴዲየም ለ11 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የቤንች ሸኮ ዞን የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና በቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
በማጠቃለያው ላይ የተገኙት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርት ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖሊትካዊ መስተጋብርን በማጠናከር ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አንስተው ይህንን የበለጠ ማጠናከር እና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ስፖርት ጤናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢኮኖሚውም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ገልፀው ባደጉት አገራት ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
ተጫዋቾች ስፖርታዊ ጨዋነት ባለው መልኩ ተጫውተው መጨረሳቸው የሚደነቅ ነው ብለው ምስጋናም ይገባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
በቀጣይ ከወረዳ ጀምሮ በተጠናከረ መልኩ የስፖርት ምክር ቤቶችን በማጠናከር በቀበሌ ደረጃ ጭምር የስፖርት ማዘውተሪያን በማመቻቸት ተጫዋጮችን ብቁ በማድረግ ጠንካራና ተወዳዳሪ ክለብ ለመፍጠር በትኩረት እንሰራለንም ነው ያሉት።
አቶ ጌታቸው ኮይካ የቤንች ሸኮ ዞን ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ሀላፊ በበኩላቸው ስፖርት የህዝቦችን አንድነት ና ወንድማማችነት ከማጠናከር ባሸገር ተግባብቶ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ድንቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 11 ቀናት በተካሄደው ዞን አቀፍ የእግር ኳስ የክለቦች ሻምፒዮና ስፖርት 10 ክለቦች መሳተፋቸውን ገልፀው በአጠቃላይ 272 ልዑካን በስፖርቱ መገኘታቸው ገልፀዋል።
አቶ ጌታቸው ስፖርት ውድድሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በማጠቃለያው ፕሮገራሙ በሲዝ ከተማና በቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ በተካሄደው ውድድር ፖሊስ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
ለደረጃ ጉራፈርዳ እግር ኳስ ክለብና የደቡብ ቤንች ወረዳ እግር ኳስ ክለብ ባደረጉት ጫወታ የደቡብ ቤንች በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃ መያዙን የቤንች ሸኮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
