





በቻይና ጉብኝት እያደረገ የሚገኘውና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ የተመራው ልዑክ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ጋር የልምድ ልውውጥ ውይይት አድርጓል።
አቶ አደም ፋራህ በልምድ ልውውጡ፥ ብልጽግና አዲስ ፓርቲ ቢሆንም በመላ ሀገሪቱ መዋቅር ዘርግቶ የተደራጀ ስራ ለመስራትና የአባላቱን አቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መልካም ውጤት ማስመዝገቡን የገለፁት አቶ አደም፤ በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከመቶ ዓመት በላይ ልምድ ካለው ፓርቲ ተሞክሮ ለመቅሰም ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።
የሲፒሲ ኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ምክትል ሚኒስትር ሺ ቺፋንግ በበኩላቸው፥ የሲፒሲ የኦርጋናይዜሽን አሰራር ስርዓት እና አጠቃላይ ሁኔታውን በሚመለከት ተሞክሮዎችን አጋርተዋል።
ዲፓርትመንቱ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ የሲፒሲ አባላትን ከላይ እስከ ታች ለማደራጀት፣ አቅማቸውን ለማልማት እና በቀጣይነት አቅማቸውን ለመገንባት እያደረጋቸው ያሉ ዋና ዋና ስራዎች እንዲሁም እያገኛቸው ያሉ ውጤቶች እና በቀጣይም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከላይኛው የፓርቲ መዋቅር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ለመዘርጋት የሚሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው፥ ብልጽግና ፓርቲ ከአደረጃጀት አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን አጋርተዋል።
በተጨማሪም በተለይ የአቅም ግንባታና የአባላት ልማት፣ የፓርቲ መዋቅርን ማጠናከር እንዲሁም “በዲጂታል ፓርቲ” ግንባታ መስክ ቴክኖሎጂን አልቆ መጠቀም የሚችል ፓርቲ እንዴት መገንባት ይቻላል በሚለው ዙሪያ ላይ በቀጣይነት አብሮ ለመስራት እና ይበልጥ እየተደጋገፉ ለመቀጠል ጥሪ አቅርበዋል።
የሲፒሲ የዲፓርትመቱ ሃላፊም በእነዚህ ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ዝግጁነታቸውን መግለፃቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
