


ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ12 ነጥብ 14 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት በላይ በ18 ወራት የስራ ኮንትራት ወል ለማጠናቀቅ በ2012 ዓ ም ወደ ስራው የተገባው ይህ ኘሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ ቢሆንም የካቲት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል።
ከመቱ-ማሻ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር “የኮንዳክተር” ዝርጋታ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የመቱ-ማሻ መስመር ዝርጋታ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አሳዬ ተናግረዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተገነባ ያለው ይህ ኘሮጀክት ከውል አንጻር የዘገየ ቢሆንም አሁን ላይ ዋናው ተቋራጭ ሦስት ንዑስ ተቋራጮችን አስገብቶ ስራውን እያፋጠነ እንደሚገኝ ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት።
አሁን ባለው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኮንዳክተር ዝርጋታው መሸፈን ከነበረበት 174 የብረት ምሶሶዎች መካከል 173ቱ የተጠናቀቀ ሲሆን 70 ኪሎ ሜትር ከሚሸፍነው የሽቦ ዝርጋታ መካከል 56 ኪሎ ሜትር ዝርጋታ መጠናቀቁንም ኃላፊው አብራርተዋል።
አካባቢው ጥብቅ ደን ያለበት መሆኑ ስራውን እንዳጓተተ ያስታወሱት ኃላፊው ይህም በባለድርሻ አካላት ቀና ምላሽ እልባት አገኝቶ አሁናዊ ጠንካራ አፈጻጸም መመዘገቡን ተናግረዋል።
የሳብስቴንሽን ግንባታ ተጠናቆ መስመር ለማገናኘት ዝግጁ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው እስከ የካቲት 30/2017 ዓ/ም ይጠናቀቃሎ ብለዋል።
የግንባታውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ የዓለም ባንክ በቅርበት ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ነው ተብሏል።
