



የወባ በሽታ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል የመከላከልና መቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
የወባ በሽታ ጫናን ለመቀነስ የሚያግዝ ሀገር አቀፍ ሳይንሳዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ትናንት በተጀመረውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ የማህበረሰብ ችግር እየሆነ መጥቷል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በወባ በሚያዙ ህሙማን ላይ ከሚከሰት የሞት ምጣኔ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው በአፍሪካ እንደሚመዘገብ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸውን ከ200 በላይ ወረዳዎች በመለየት የበሽታውን ጫና ለመቀነስ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ የወባ በሽታ ልየታና ህክምና ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በበሽታው የሚያዙ ዜጎችን ቁጥር በ50 በመቶ ለመቀነስ ዕቅድ ተይዞ ከ52 በመቶ በላይ መቀነስ እንደተቻለ አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባደረገው ርብርብ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወቅታዊ መረጃ ለማግኘትና ምላሽ ለመስጠት አሁናዊ መረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ወባን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች ላይ የምርምርና ፈጠራ ስራዎችን በመስራት ለፕሮግራም ግብዓት የሆኑ ምክረ ሃሳቦችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ የምርምር ስራዎችን ከተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተለያዩ ተቋማትና ተመራማሪዎች የተሰሩ የምርምር ውጤቶች ተጨምቀው ተግባር ላይ እንዲውሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ጉባኤው ከወባ ነፃ ሀገር ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ የሚያግዙ የፖሊሲ ግብዓቶች የሚለዩበት የምክክር መድረክ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባና ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶክተር ገረመው ጣሰው ኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተሰራው የቅንጅት ስራ የበሽታው ስርጭት መቀነስ እያሳየ መሆኑን ጠቁመው በሽታው በከፍተኛ መጠን የሚጨምርበት ወቅትን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች አሁንም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
