




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ እንደገለፁት ክልሉ ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት መሆኑን ጠቁመው ከቀድሞው ክልል የተረከባቸው በርካታ የመሠረተ ልማት ዕዳዎች መኖራቸውን ተናግረዋል ።
የክልሉን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተመቻቸ ለማድረግ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የግድ በመሆኑ መንግስት አቅዶ ከሚሰራው ባሻገር አጋዥ ፕሮግራሞች አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በሚገባ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የስትሪንግ ኮሚቴ የሚሰጠው ድጋፍ ለስራው አጋዥ በመሆኑ ቴክኒካል ሥራዎችን መምራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ በማችንግ ፈንድ የሚፈለገው ብሎ ያስቀመጠው ከዶላር ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ከፍ እያለ በመሆኑ ከሚመለከታቸው ጋር መምከር ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ፋጂዮ ጠቁመዋል።
በመንገድ ሥራ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥንካሬውን በመውሰድ በፕሮግራሙ የተሻለ ሥራ በመስራት የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መሄድ ይገባል ሲሉ አቶ ፋጂዮ አሳስበዋል።
ፕሮግራሙ በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሥር ለ5 ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ዋና አላማ የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገድ በማገናኘት አርሶና አርብቶአደሩን የሚያመርተውን ምርት ወደ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ህይወት እንዲኖረው መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የሁሉን አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ጌዲዮን እስጢፋኖስ በፕሮጀክቱ የሚሰሩ ሥራዎች ለኮሚቴው አቅርበዋል።
በፕሮጀክቱም የአዳዲስ የመንገድ ግንባታዎች ፣ የመንገድ ጥገና ስራዎች፣የመንገድና የስትራክቸር ሥራዎች ፣ከዲዛንና የአማካሪ ማህበራት የሚያከናውን የተለያዩ ሥራዎች መሆናቸውን ኢንጂነር ጌዲዮን ጠቁመዋል ።
የስትሪንግ ኮሚቴ አባላትም በሰጡት አስተያየት ለማችንግ ፈንድ የሚያዝ ገንዘብ ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ከባለድርሻ አካላት ጋር ብዙ ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ህዝቡን ያሳተፉ መሆናቸው ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
የሚሰሩ ሥራዎች ጥራትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ በፕሮግራሙ ማንዋል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ስትሪንግ ኮሚቴው ሥራዎችን በመስክ ምልከታም ማየትና አስተያየት መስጠት ይገባዋል ብለዋል።
