
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ከጅቡቲ የመሰረተ-ልማትና ኢክዩፕመንት ሚኒስትር ሀሰን ሀሙድ ኢብራሒም ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም ሁለቱን አገራት በመሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው የዲኪል-ጋላፊ መንገድ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት እና በቀጣይ ምዕራፍ የሚሰሩ ስራዎች ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም በቅርቡ በአራቱ የቀጣናው ሀገራት ስምምነት ይፋ የሆነው የኮሪደር ማኔጅመንት ባለስልጣን በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ህብረት የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ እንዲካተትና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ማጉላት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
