በመኧን ማህበረሰብና በኮንታ ኮይሻ ነዋሪዎች መካካል የተደረገው እርቀ ሰላም የነበረውን ጥላቻ በማስወገድ የእርስ በእርስ መስተጋብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ፡፡

Spread the love

ነዋሪዎቹ እርቀ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆንም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመኧን ማህበረሰብና በኮንታ ኮይሻ ነዋሪዎች መካካል ለዘመናት ዘልቆ የነበረው ችግር በእርቀ ሰላምና በይቅርታ ተፈትቷል ፡፡

በነበረው የይቅርታና እርቀ ሰላም ስነ ስርዓት ከሁለቱም ወገኖች በኩል የሀገር ሽማግሌዎች፣ሀይማኖት አባቶች፣የጎሳ መሪዎችና ባላባቶች እንዲሁም የክልልና የዞን ፣የወረዳ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ስነ ስርዓቱ ተከናውኗል ፡፡

በተከናወነው ስነ ስርዓት ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካካል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የተደረገው እርቀ ሰላም የነበረውን ጥላቻ በማስወገድ የእርስ በእርስ መስተጋብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

አስተያየት ከሰጡት መካካል ወ/ሮ አስቴር አስፋው የኮንታ ኮይሻ ነዋሪ ሲሆኑ የተደረገው እርቀ ሰላም የህዝቦችን አንድነትና ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላይኛው ተሳታፊ ከመኧን ማህበረሰብ አቶ ጥጋቡ መንገሻ ሲናገሩ የነበሩ ችግሮች በእርቅ መፈታታቸው አንድነታችንን ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል ፡፡ ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩም ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ወጣቶችን ሰብስበው እንደሚመክሩም አቶ ጥጋቡ ተናግረዋል ፡፡

አቶ በለጠ በዛብህ ከኮንታ ኮይሻ የተሳተፉ ሲሆን እርቀሰላሙ እንዲደረግ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር ተናግረዋል ፡፡ እርቀ ሰላሙ ይፈጻማል የሚል እምነት እንዳልነበራቸውና የክልሉ መንግስት በሰጠው ትኩረት በመከናወኑ ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል ፡፡ በቀጣይነትም ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ከመአንና ከኮንታ ኮይሻ ማህበረሰብ ጋር የተጠናከረ ግንኙነቶችን በማጠናከር ዘላቂ እንዲሆን በቅንጅት እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል ፡፡

የእርስ በርስ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉም አቶ በለጠ ጠይቀዋል ፡፡

ባላባትሞርባ ዙንቁ ከሰላማጎ ወረዳ የመጡ ተሳታፊ ሲሆኑ እሳቸውም ከእርቅ ስነ ስርዓት በኋላ ወደ መጣንበት ተመልሰን ህብረተሰቡን በማስተማር ዳግም ችግሮች እንዳይከሰቱ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል ፡፡

የመንገድ ከፈታ አለመኖር ችግሮች በዘላቂነት እንዳይፈታ አንዱ ምክንያት ነው ያሉት ሞርባ ዙንቁ ይህንን ችግር መንግስት ቢፈታልን እርስ በርስ ግንኙነቶች ይበልጥ ተጠናክረው የወንጀል ድርጊት እንዲቀረፍ ያስችላልም ብለዋል ፡፡

እርቀ ሰላሙ መደረጉ በወዳጅነት መካከል ጠላትነትን የሚያስቀር መልካም ተግባር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሰላሙ ዘላቂነት እንዲኖረው ሁሉም በቅንጅት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል ፡፡

በመኤን ማህበረሰብ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ኦይጳይ ቦሹ አሁን ያወረድነው እርቀ ሰላም ችግሮቻችንን ውሃ ይዞት እንደሚሄድ ነገር ይሁን በማለት በአካባቢያችን የሚታዩ የመሠረተ ልማት ችግሮች በርካታ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው በመኧን ማህበረሰብና በኮንታ ኮይሻ ነዋሪዎች መካካል የተደረገው እርቀ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በአካባቢው የተጓደሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሟሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲሟሉ ጥረቶች ይደረጋሉ ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *