



በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሂደት የሚከናወኑ ተግባራትን እንደሚደግፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት ገለጹ።
የድርጅቶቹ ተወካዮች በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ስራዎችን መደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ተገኝተዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) መንግስት ዘላቂና አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ የውይይት ባህልን ለማጎልበትና በተለይም ወጣቱ የሰላም ባለቤት እንዲሆን የሚያስችሉ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ስራ ተግባራትን በስፋት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የሰላም ግንባታ ስራ የበርካታ አካላትን ቅንጅት እንደሚፈልግ ጠቅሰው የተመድ ድርጅቶች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ቸሩጌታ ገነነ በበኩላቸው ግጭቶች በሰላማዊ መንገድና በዘላቂነት እንዲፈቱ ማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ባለፉት 11 ወራት ከ700 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱና ከሕብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን ጠቁመዋል።
የተመድ ድርጅቶች ተወካዮች በበኩላቸው መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕን ጨምሮ እያከናወናቸው ያላቸውን ተግባራት አድንቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ስራም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማቱ የሰላም ሚኒስቴር የሚያከናውናቸውን የሰላም ግንባታ ስራዎችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የመመለስ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
