ምክር ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት 17.6 ቢሊዮን ብር ሆኖ የቀረበውን ረቂቅ የበጀት አዋጅ አጸደቀ።

Spread the love

ረቂቅ የበጀት አዋጁን የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ለምክርቤቱ አቅርበዋል።

የቀረበው በጀት ከክልል ገቢ የሚሰበሰብ፣ከፌዴራል መንግስት ድጎማና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሚገኝ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አብራርተዋል ።

በዚህም መሠረት ለክልል ማዕከል መ/ቤቶች መደበኛና የካፒታል ወጪ 1.5 ቢሊዮን ፣

ለዞኖች ጥቅል በጀት 14.5 ቢሊዮን ፣

ለክልላዊ ፕሮግራሞች 995.6 ሚሊዮን ፣

ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 434.7 ሚሊዮን

ለክልሉ መጠባበቂያ በጀት 120 ሚሊዮን በአጠቃላይ የ2017 በጀት ዓመት 17ቢሊዮን 622 ሚሊዮን 088 ሺህ 402 ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ክብርት ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ለምክርቤቱ አቅርበዋል ።

የበጀት ምንጩ ከፌዴራል መንግስት ግምጃቤት ፣ከውጭ እርዳታ ፣ከዘላቂ ልማት ግቦች 7.1 ቢሊዮን፤ ከመደበኛ ገቢ፣ከጤና ተቋማት፣ከማዘጋጃ ቤት ገቢ፣ከትምህርት ቤቶች ገቢና ከቴሌቶን ገቢ 10.4 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበሰብም ሰብሳቢዋ አብራርተዋል።

በቀረበው ዝርዝር የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ በምክር ቤቱ አባላት አስተያየቶች ተነስተዋል ።

የምክርቤት አባላት ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በጀት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ያለማሳየቱ የወቅቱን የገበያ ሁኔታና የዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ለክልሉ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ለቀጣይ ታሳቢ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ከፌደራል ግምጃ ቤት የሚመጣዉን በጀት ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነዉ፤ገቢ ላይ የተሰጠወ ትኩረት የሚደነቅ ሆኖ የተሻለ ለመሰብሰብ አሁንም ተጨማሪ ስራ እንደሚያስፈልግ አስተያየት ቀርቧል።

በረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ሀሳብ እና አስተያየት የሰጡት የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው የቀረበው የ2017 በጀት ውጤታማ እንዲሆን ክልላዊ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም ገቢ መሰብሰብ ይገባል ብለዋል።

በጀቱንም ለሰብዓዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም ከሌብነት፣ከብክነትና ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ የፋይናንስ መመሪያና ደንብን ተከትሎ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል ።

የክልሉ መንግስት ፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በሰጡት ምላሽ የክልሉን ገቢ ለመሰብሰብ ያሉንን የገቢ አማራጮች በመጠቀም ግቡን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በ6ኛ ዙር 3ኛ የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤ የቀረበው የ2017 በጀት ዓመት 17.6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የቀረበውን ረቂቅ በጀት አዋጅ የምክርቤት አባላት በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *