
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ነዋሪዎች በትምህርት ቤት በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ።
በወረዳው ኬንቾ ቀበሌ ዛሬ ጠዋት ንጋት ላይ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቀጥር 55 መድረሱንም ፖሊስ ገልጿል።
የጎፋ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ታረቀኝ አጥናፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ትናንት ሌሊት ለ5 ሰዓታት ሳያቋርጥ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ዛሬ ንጋት ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ አስከትሏል።
በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰትም ነዋሪዎችን በአቅራቢያ ባለ ትምህርት ቤት በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመንግስት አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ለሟች ቤተሰቦች የዕለት ደራሽ ምግብ በማድረስ እያጽናኑ መሆናቸውንም ኢንስፔክተር ታረቀኝ ተናግረዋል።
የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊጨምር እንደሚችል ያመለከቱት የፖሊስ አዛዡ፣ በህብረተሰቡ እና በፀጥታ ሀይሎች እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
