
በመጪው 18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት ቃል ኪዳን የሚታደስበት ልዩ ዕለት ሆኖ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በሰጡት መግለጫ፣ ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ የህዝቦቿን አንድነትና የማይደፈር ሉዓላዊነቷን የሚያመለክት የተቀደሰ አርማ መሆኑን ገልጸዋል።
አፈ ጉባዔዉ በመግለጫቸዉ የዘንድሮ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!”በሚል መሪ ቃል ይከበራል ብለዋል።
አፈ ጉባዔው “ለዚህ ክቡር ሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠትና ይህንን የሀገር ፍቅር ስሜት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” በማለት የዕለቱን ትልቅ ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚሁ መሠረት መጪው ሰኞ ጥቅምት 03 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:30 ላይ በመላው ክልሉ በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና የህዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ሠንደቅ ዓላማ በክብር ይሰቀላል። ህዝቡም በሠንደቅ ዓላማው ፊት በመቆም ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ቃል ኪዳን በቃለ መሐላ ያረጋግጣል።
የክልሉ ምክር ቤት መላው የክልሉ ህዝብ፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሠራተኞችና የጸጥታ አካላት በዚህ ታሪካዊ ዕለት በሚከናወኑ ዝግጅቶች ላይ በነቂስ በመውጣት ለሠንደቅ ዓላማችን ያላቸውን ክብር እንዲገልጹ ጥሪ አቅርቧል።
