
በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ የማድረጉን ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ዲጂታል መታወቂያ መስጠት መጀመሩን ከአንድ ወር በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ዲጂታል መታወቂያው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በተደራጀ አግባብ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገድ ከጀመረች 40 ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1 ሚሊየን 100 ሺህ በላይ ስደተኞችን በ27 ስደተኛ ጣቢያዎች ከለላ ተሰጥቷቸው እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
መንግስት ከለላ ላደረገላቸው ስደተኞች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ማህበራዊ አግልግሎቶችን እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከስደተኞች ጋር በተያያዝ ያለው የመረጃ አያያዝ በሚፈለገው ደረጃ ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ አለመሆኑ ደግሞ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ላይ እክል ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መንግስት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ዲጂታል መታወቂያ መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ የማድረጉን ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
ለስደተኞት የሚሰጠውን ዲጂታል መታወቂያ ከተቋሙ የስደተኞች አስተዳደር ሲስተም ጋር በማስተሳሰር የተደራጀ የመረጃ አያያዝ እንዲኖር ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ይህም በሀገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
