ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ የክልሉ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

Spread the love

የቢሮው ሀላፊ ዶ/ር ዐብይ አንዴሞ ቢሮው በክልሉ በ2018 በጀት አመት 10 ወራት ውስጥ የዜጎችኝ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።

ሀላፊው አክለውም ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በግብርና፣በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች በአጠቃላይ ለ62 ሺ 72 ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም አብራርተዋል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዳዊት ወንድሙ በበኩላቸው ቢሮው ከፋይናንስ አቅርቦት አንፃር 694 ሚሊየን 186 ሺ 27 ፋይናንስ በማቅረብ ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡም መደረጉን ገልጸዋል።

በመስሪያና መሸጫ አቅርቦት ዙሪያ 5 ሺ 595 ሄክታር መስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም 87 መስሪያና መሸጫ ሼዶችን ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል።

ለኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ 168 ሚሊየን 411 ሺ 359 ብር የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል።

በሜካናይዜሽን እርሻ ለወጣች የስራ ዕድል ለመፍጠር የክልሉ መንግስት 15 የእርሻ ትራክተሮችን ገዝቶ ለዞኖች በማውረድ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አቶ ዳዊት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በየአካባቢው የመኖ ማቀነባበሪያ በማመቻቸት የሌማት ትሩፋት ዘርፍን ውጤታማነት ለማላቅና በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቢሮው እየተጋ መሆኑ ተመላክቷል።

ቢሮው GHUCC ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ስራ አጥ ዜጎችን በማሰልጠንና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት በተለያዩ ዘርፎች ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል።

በመጨረሻም ወጣቶች በሚሰጣቸው ስልጠና መሠረት የተመቻቸላቸውን የብድር አገልግሎት በመጠቀም የተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑም አሳስበዋል ሲል ደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *