የተማሪ ውጤት ለማሻሻል የመምህራን ሚና የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

Spread the love

የትምህር ስብራትን ለመጠገንና ጥራት ያለውን ትምህርት ለህፃናት በመስጠት የተሻለ ውጤት ለማምጣት በመምህራን ልማትና አቅም ግባታ ላይ ዘርፌ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመምራንና ትምህርት ልማት አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ ገለጸዋል ።

የትምህርት ጥራት መረጋገጥና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ስታሰብ የመምህራን አቅምና ተነሳሽነት ትልቅ ቦታ እንደሚይዝ ያነሱት አቶ ማርቆስ፤ በሀገር ደረጃ የመምህራንን አቅም፣ ጥራትና ተነሳሽነትን ለማሻሻል የሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራርን አቅም ለመገንባት በሁለት ክረምንት ለ120 ሰዓት በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነትና በስነ ዘዴ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በ2016 ዓ/ም ክረምት የአቅም ግንባታ ስልጠና ወስዶ የሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ከወሰዱት አጥጋቢና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡ መምህራን ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጨመሩን አንስተው በ2017 ዓ/ም ክረምቱን ስልጠና የወሰዱት በዚህ ዓመት እንደሚፈተኑና የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ይዘትን ጠንቅቆ ከመረዳትና ህፃናትን የማስተማሪያ ስነዘዴ በአግባቡ ተረድቶ ከማስተማር አንጻር በ1ኛ ደረጃ መምህራን አቅም ላይ የሚታየውን ጉድለት ለመሸፈን በክልል ደረጃ ጠቅለል ያለ የትምህርት ይዘት በማዘጋጀትና ስነ ዘዴ ላይ ከዩንቨርስቲዎች እና የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት ዝግጅት ላይ መሆኑን አክሏል።

ተከታታይ ሙያ ማሻሻያ መምህራን በስራ ላይ እያሉ አቅማቸውን ለማሻሻል ሚናው ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ ከክትትልና ድጋፍ ማነስና ለስራው ዋጋና ትኩረት ሰጥቶ ከመምራት ጉድለት መታየቱን ጠቁመዋል።

ይህን ለመቅረፍ ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስራ በዕቅድ እየተሰራ መሆኑን በማንሳት መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ስነዘዴ፣ ምዘና እንዲሁም የክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደትን ከመምራት ሙያውን በተከታታይነት ለማሻሻል በዚህ ዓመት በልዩ ሁኔታ አቅደው እንዲሰሩ መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት ከሙያው ዘርፍ የሚወጡ መምህራርንን ከመተካትና እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ለመሙላት አዳዲስ ዕጩ መምህራንን መልምሎ ከማሰልጠን አንጻር 800 መምህራንን ከቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ጋር በተለያዩ የትምህርት ዓይነት ለማሰልጠን ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ማርቆስ ገልጸዋል ።

ከነዚህም ዕጩ መምህራን 60% በዲፕሎማ ሲሆን 40%በቅድሜ 1ኛ ደረጃ ስልጠና እንደሚሰጣቸው በመግለጽ በአርብቶ አደር አካባቢ ያለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ ከተሰጠው ኮታ በተጨማሪ 100 ሰልጣኝ በልዩ ሁኔታ የትምህርት ዕድል እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ለመምህራን በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጠው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በክልሉ ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በሚሰጠው ድጋፍና ክትትል በዞን፣በወረዳ ብሎም በትምህርት ቤት ደረጃ የሚሰጠው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

በአጠቃላይ የትምህርት ጥራትና የተማሪ ባህሪ መሻሻል ሲታሰብ የመምህራን ተነሳሽነትና ለሙያው ያለው ፍቅር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የጠቆሙት አቶ ማርቆስ መምህራን ለትውልድ ቀረፃ እና ትምህርት ለሀገር ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽጾ አንጻር ይህን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የባለድርሻ አካላት በመምህራን ልማት የየድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በየደረጃው ያለውን የመምህራን የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ለመፍታት በጥናትና በውይይቱ መለየቱን ያስታወሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው በከተሞች የቤት መስሪያ ቦታና በገጠር ቤትን ከማመቻቸት በትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በከተማ በህብረት ስራ በማደራጀት በሊዝ መነሻ ዋጋ መሬት የሚቀርብበት ሂደት ላይ በየደረጃው ካሉት ከዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የባለድርሻ አካላት ጋር ውል መፈራረሙን፤ መሬት እያገኙ መሆኑን፤ በገጠር በህብረተሰቡ ተሳትፎ ነባር ቤት ዕድሳትና አዲስ ቤቶች እንዲገነቡ በዕቅድ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው አንስተዋል።

የደመወዝና ደረጃ ዕድገት ጉዳይን በሚመለከት አብዘኛው በተሰራው ስራ መፈታቱን በማንሳት በተወሰኑት ቦታዎች ያለውን ውዝፍ የደረጃ ዕድገትን ከአዲሱ ደመወዝ ጭማሪ አስድሞ በትኩረት እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት መሆኑን አብራርተዋል።

ከሀብት ውስንነት የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን የደመወዝ መዘገየት በተደረገው ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ምክክር እየተቀረፈ መምጣቱን፤ የዝውውርና መሰል ጉዳዮች በቅርበት እየተፈቱ መሆኑን አንስተዋል።

በመጨረሻም የትምህርት ጥራት ያለው፣ ጠንካራና ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥ በመምህራን ላይ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስራ መስራትና የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተከታትሎ መፍታት፤ መምህራን ራሳቸውን ሁሌ ከወቅቱ ጋር ማዘጋጀት እንደሚገባ አቶ ማርቆስ አስገንዝበዋል ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *