የዳውሮ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ለማልማት፣ ለማሳደግ እና ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ህዝቡንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለፀ።

Spread the love

የዳውሮ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ለማልማት፣ ለማሳደግ እና ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ህዝቡንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠራ እንደሚገኝ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ገልጸዋል።

የብሄሩን ባህል፣ ታሪክና ምርምር ማዕከል ለማስገንባት ህዝባዊ ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሚገኝና በሂደቱም ሰፊውን ህዝብ፣ የልማት አጋሮችን እና ወዳጆችን በማሳተፍ በተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በ 2 ወር ጊዜ ብቻ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ተግባሩ የዞኑን ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድነትን የፈጠረ፤ የዞኑ ተወላጆችና የልማት ደጋፊዎችን መካከል ቁጭት የጫረ ሲሆን ተሳትፎው አስደናቂ በሆነ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የባህል፣ ታሪክና ምርምር ማዕከል አካል የሆነውን አዳራሽ ግንባታ በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ ለአገልግሎት በማብቃት እንዲሁም ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገር በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ዳዊት አስገንዝበዋል።

አስተዳዳሪው እንዳብራሩት ይህንን ዕቅድ ለማሳካት በዞኑ ለሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮችና አደረጃጀቶች የሀብት ማሰባሰብ ዕቅድ ተሰጥቷቸው እየተሰራ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ እና ከዞኑ ውጪ የሚገኙ የዳውሮ ተወላጆች፣ ዳያስፖራዎች፣ የልማት አጋሮች እና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተግባሩ ላይ ለማሳተፍ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት ባለፉት 2 ወራት በተደረገው ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ከ10,000,000 ብር በላይ ገቢ ተሰብስቦ (አስር ሚሊዮን ብር ) በዳውሮ ልማት ገቢ ማሰባሰቢያ አካውንት ገቢ ተደርጓል።

አቶ ዳዊት አሁን ለተገኘው ስኬት በዞኑ ህዝብና አስተዳደር ስም በሂደቱ ለተሳተፉ እና አየተሳተፉ ለሚገኙ ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረባቸዉን የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

የዞኑ ህዝብ፣ ከዞኑ ውጪ የሚገኙ የብሄሩ ተወላጆች፣ የልማት አጋሮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በዞኑ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች እና ዳያስፖራዎች ያልተቆጠበ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንድትቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *