በክልሉ በተገኘው ሠላም፣ የገጠርና የከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ ጨምሯል፦ አቶ አንድነት አሸናፊ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ “ዘላቂ ሠላም ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መር ቃል የ2016 ዓ/ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የሴክተር ጉባኤ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

በክልሉ ዘላቂ ሠላምና በማስፈን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በ2016 በጀት ዓመት የባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገብ ነው የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ የገለጹት።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የፀጥታ ችግር የነበረባቸውን የአርብቶአደር አከባቢዎች ላይ ሠላምን በማስፈን ተቋርጦ የቆየውን የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ዳግም በማስጀመር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከር ተችሏል።

ክልሉ ከጎረቤት የውጭ ሀገር ጋር ድንበር በሚጋራባቸው ቀጠናዎች የሚከሰቱ ወንጀሎችን 70 ከመቶ በውስጥ አቅም መመከት መቻሉን ያብራሩት አቶ አንድነት በከተማና ገጠር የሚከሰቱ መደበኛ ወንጀሎችን በመቆጣጠር በክልሉ ሠላማዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማስቀጠል መቻሉን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የህዝብ አደረጃጀት በማጠናከር በፀጥታ መዋቅር ቅንጅት በተሰራው ጠንካራ ሥራ በክልሉ ከተወሰኑ የአርብቶአደር ቀበሌያት በስተቀር በሁሉም አካባቢ ተንቀሳቅሶ የልማት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ እና የፖለቲካ ስራዎች በነጻነት ማከናወን መቻሉንና በዚህም በክልሉ በተገኘው ሠላም የገጠርና የከተማ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ መጨመሩን ገልጸዋል።

የተሻሉ አፈጻጸሞችን በማጠናከር በተያዘው በጀት ዓመት በተወሰኑ የአርብቶአደር ቀጠናዎች ያለውን የፀጥታ ችግር በመቅረፍ አከባቢዎችን ወደ አስተማማኝ ሠላም በማሸጋገር በአከባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በሙሉ አቅም ወደ ልማት ለማስገባት በትኩረት እንደሚሰራም ነው ኃላፊው የገለጹት።

አስተማማኝ የሠላምና ፀጥታ አደረጃጀት በመፈጠር መደበኛ ወንጀሎችን የመቆጣጠር ተግባር በማጠናከር በክልሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የክልሉን ብልጽግና በጽኑ መሠረት ላይ ማጽናት እንደሚገባም ኃላፊው አቶ አንድነት የጠቆሙት።

ዝርዝር የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፓርት በቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ ታምሩ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት የህግና የፍትህ ጉዳዮች ቋም ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አምሳሌ ንጋቱን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሁሉም ዞኖች የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *