የትምህርት ሴክተር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተተገበረ ያለው ማሻሻያ አውንታዊ ለውጥ እያሳየ ይገኛል፦ ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

Spread the love

መንግሥት የትምህርት ሴክተር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተገበረ ያለው ማሻሻያ አውንታዊ ለውጥ እያሳየ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ”የትምህርት ጥራት እምርታ ለሁለንተናዊ ብልጽግና!” በሚል መርህ ቃል በተዘጋጀው የትምህርት ሴክተር ጉባኤ ላይ ነው።

ትምህርት የሀገር ተረካቢ የሆኑ ዜጎች በእውቀት፣በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጸው የሚወጡበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉት ጊዜያት በትምህርት ሽፋን ላይ ተኩረት ተደርጎ በተሰራው ስራ ተደራሽነትን ማስፋት ቢቻልም የጥራት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግሥት ይህንን መሠረታዊ የትምህርት ሴክተር ችግር በውል በመለየት በፖሊሲና በህግ ማዕቀፎች ጭምር በመታገዝ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሰጠው ልዩ ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።

ከእነዚህ የማሻሻያ ማዕቀፎች አንዱ በሆነው የትምህርት ቤት የደረጃ ማሻሻያ ንቅናቄ በክልሉ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የመምህራንና የትምህርት ሴክተር አመራሮች ብቃት ማሻሻያ የአቅም ግንባታ ስራው በቀጣይነት ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የትምህርት ጥራትን በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ እየተሰራ ባለው ተግባር አንዱና ዋነኛ ማነቆ በአንደኛ ደረጃ የመማሪያ መጻሕፍት ተደራሽነት ችግር መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ከትምህርት ሚኒስትር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የአቅም ግንባታ ስራው ቀጣይነት ኖሮት ውጤታማ እንዲሆን በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ በማጠናከር በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማትን በቴክኒክና በቁሳቁስ መደገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆል አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ የማሟላት ተግባር ልዩ ትኩረት ይሻል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በትምህርት ጥራት ላይ የተጀመረው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ የትምህርት ሴክተር አመራሮች ሙሉ የሥራ ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት በማድረግ የመማር ማስተማር ተግባሩን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ትምህርት ሁለንተናዊ የሀገር ዕድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን የገለጹት የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ይህንን ለማሳካት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ተደራሽ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ደኤታዋ አክለው ለትምህርት ስብራት ማነቆ ከኾኑት ውስጥ በዋናነት የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ውስንነት፣ የትምህርት አመራር ቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ያለመሆን እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት በሰጠው ትኩረት ለአብነት ከ2015 በጀት ዓመት ማገባደጃ ተግባራዊ በኾነው ”ትምህርት ለትውልድ ” ንቅናቄ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ የትምህርት ቤት ዕድሳት በማድረግና ግብዓት በማሟላት ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በክልሉ የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት ሚኒስትር ደኤታዋ በተላይ የትምህርት ሴክተር አመራሮችና መምህራኖችን አቅም ግንባታን በመደገፍ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ሴክተር ቁልፍ ተልዕኮው የነገው ሀገር ተረካቢ ዜጋን በዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በመቅረጽ የሀገር ብልጽግናን ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አልማው ዘውዴ ከዚሁ አኳያ በሀገር እንዲሁም በክልላችን ደረጃ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ አሁንም ያልተሻገርናቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል።

የተማሪዎች የመማር ተነሳሽነት መቀነስና የትምህርት ተሳትፎ መቀነስ፣ የተማሪዎች ውጤትና የትምህርት ውጤታማነት መቀነስ የመምህራን የትምህርት ቤት አመራሮች ብቃት ማነስ፣ስምርትና መልካም አስተዳደር ጉድለቶች የአንደኛ ደረጃ መጽሐፍት ህትመትና ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆን፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት በቂ ትኩረት ያለማግኘት የቀጣይ ጊዜ ተግባራችን ጊዜ የማይሰጡ እና ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ እየተተገበሩ ያሉ የትምህርት ሴክተር የለውጥ ማሻሻያ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አልማው የተጀመረው ጥረት የተፈለገው ውጤት እንደሚያመጣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአጽንኦት ጠይቀዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *