ከ294 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

Spread the love

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከ294 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታውቋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት ኮሚሽኑ ከጥቅምት 22 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል መሆኑንም ገልጿል፡፡

በዚህም 279 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የገቢ እና 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች፤ በድምሩ 294 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን ነው የተገለጸው፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደገኛ እጾች፣ መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ብሏል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 14 ተጠርጣሪዎች እና 7 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቁሟል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በበረራ መያዛቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *