








በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች በቦንጋ ከተማ ተከብሯል፡፡
“የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ለዕለቱ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ሰነድ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ቀርቦ በሰፊው ውይይት ተደርጓል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ለዕለቱ ውይይት ባቀረቡት ሰነድ እንዳገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ችግሮችን ተሻግራ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሏን ገልጸው ከእነዚህ አንዱ እንደ ሀገር የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከሪፎሪሙ በኃላ በኢኮኖሚ ዘርፍ የተመዘገቡት ሁኔታዎች መኖራቸውንና በተለይም በግብርና ፣በኢንዱስትሪ፣ በአይ ሲ ቲ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ ፣በቱሪዝምና በማዕድን ላይ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊና ክልላዊ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣የኑሮ ውድነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ና ከውጭ ሊገቡ የሚችሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት የሪፎርሙ ማዕቀፎች አንጸባራቂ ውጤት እያስመዘገበን እንገኛለንም ብለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ የተገኙ ውጤቶች በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዥ በመሆናቸው በክልሉ ያለውን ሀብት በተገቢው በመጠቀም ከዚህ በላይ ተሻግሮ ለመሄድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ ለማልማት የሚያስችል ሰፊ ፀጋ ያለበት ክልል ያለበት በመሆኑ በተገቢው ተጠቅመን በቂ ሀብት ለመፍጠር በጋራ ማሳብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ እስከአሁን በሁሉም ዘርፎች የተገኙ ለውጦችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት በክልሉ ያሉትን በርካታ ጥረቶችና ዕድሎችን በመጠቀም በቀጣይ ሁለንታናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በማጠቃለያው ንግግራቸው ባለፉት ጊዜያት በኢኮኖሚ ዘርፍ ያሳከናቸው ተግባራት ለቀጣይ የተሻለ የተስፋ የሚሰንቅ ነው ብለዋል፡፡
ያለፈውን ዓመት ተግባሮቻችንን በማስተወስ ለሚቀጥለው በቂ ዝግጅት በማድረግ ክልላዊ አቅም ከፍ የሚናደርግበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን ወርቅና የተለያዩ ማዕድን ሀብት በአግባቡ መቆጠጠር ከተቻለ ለሀገርም ለክልልም ትልቅ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ በቀጣይ በጥንቃቄ በመያዙን ለኢኮኖሚ አጋዥ እንዲሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ምርትና ምርታማናትን በማሳደግ ገበያን ለማረጋጋት በከተማ ግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ ሊለመድ እንደሚገባ እና ትኩረት ሰጥቶ መስራ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት በክልሉ ያለውን ምቹ የማልማት አቅም በመጠቀም ምርተና ምርታማናትን ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቦንጋ ማዕከል የክልል ሴክተር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
