“ሪፖርታዥ”

Spread the love


የክልሉን ግብርና በማዘመኑ ረገድ አይነተኛ ሚና እየተወጡ ያሉ ፕሮግራሞች!

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ብሎም የዜጎችን የስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል እና በዘርፉ የስራ ዕድል ለመፍጠር እና የኤክስፖርት ምርትን በማሳደግ ከውጭ የሚመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ዘርፌ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም አበረታች ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ፥ የክልሉን የመልማት አቅም በመለየት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስረጽ፣ ለአርሶ አደሮች ግብዓት በማቅረብ፣ በሁሉም ዘርፍ የኤክስቴንሽን ድጋፍ በማድረግ፣ የመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታና አጠቃቀም በማሻሻል፣ የግብይት ስርዓትን በማሻሻል እንዲሁም የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ከብዙ ፕሮግራሞች ጋር በቅንጅትና በትብብር እየሰራ ይገኛል።

በዛሬው ቆይታችን ከክልሉ የግብርና ቢሮ ጋር በቅንጅት ከሚሰሩት ፕሮግራሞች አንዱ የሆነውን የክልሉ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSRP) አፈጻጸም ለመቃኘት ወደድን። መልካም ንባብ፦

በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል FSRF በመባል የሚታወቀው ፕሮግራም ሙሉ መጠሪያው በእንግሊዝኛ food system Resilience program የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በአለም ባንክ ድጋፍ በምስራቅ እና ደቡብ የአፍሪካ ቀጠና በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፕሮግራም ነው።

ፕሮግራሙ የልማት ዓላማ (PDO) በተመረጡ የፕሮጀክት አካባቢዎች የምግብ ሥርዓትን የመቋቋም አቅም ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ችግር እንዳይፈጠር አስቀድሞ የመከላከልና አቅምን ማሻሻል ላይ የሚሰራ ድርጅት እንደሆነ በግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSRP) ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሁሰን ገልጸዋል ።

ፕሮግራሙ 3 ዋና ዋና እና አንድ ደጋፊ ክፍሎችን ዓላማ በማድረግ የሚሰራ ሲሆን በዋናነት የግብርና ኤክስቴንሺንን መደገፍና ማጠናከር ላይ ያተኩራል በግብርና ኤክስተንሽን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና የማስረጽ፣ ለአርሶ አደሮች ግብዓት በማቅረብ፣ በሁሉም ዘርፍ የኤክስቴንሽን ድጋፍ ማድረግ እንደሚሰራ አንስተዋል ።

ሁለተኛው በመስኖ መሠረተ ልማት በማተኮር የመስኖ መሠረተ ልማት አውታሮችን መገንባትና የተገነቡትን ወደ አገልግሎት በማስገባት አጠቃቀምን ማሻሻል ላይ በማትኮር እንደሚሰራ ጠቅሰዋል ።

ሦስተኛ ዓላማ አጠቃላይ የገበያ ልማትና መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የግብይት ማዕከላትን በመገንባት፣ አነስተኛ ድልድይ፣ መጋዘን፣ የወተትና ማር ማቀነባበሪያ ማዕከላትን
በመገንባት የገበያ ትስስር በማሻሻል እንዲሁም የአቅም ግንባታና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አበረታች ተግባራትን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል ።

በመጨረሻም ለሚሰሩ ስራዎች በየደረጃው ያሉት የስትሪንግ እና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ተገቢውን አቅጣጫ በመስጠት ድጋፍና ክትትልና ግምገማውን በተቀመጠው አሠራር መሰረት ማድረግ በመቻላቸው መሆኑን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ በክልላችን ከሐምሌ 2016 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ በመግባት ከፍተኛ አቅም ባላቸውና በተመረጡ 6 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 15 ወረዳዎች እንዲሁም በ 368 ቀበሌያት ውስጥ የሚገኙ 1,594,973 (51%ሴት) ተጠቃሚዎችን በማቀፍ እየተተገበረ ያለ ፕሮግራም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፕሮግራሙ አቀራረጽ ከቀደምት የግብርና ዕድገት ፕሮግራሞች በተገኘው ትምህርትና ልምድ ላይ የተመሰረተ ነው።

ፕሮግራሙ የሚከተላቸው ቁልፍ መርሆዎች፤ የተቀናጀ አቀራረብ ፣ ሁሉ አቀፍ እና ለስትራቴጂካዊ ግቦች ምላሽ መስጠት ፣ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እና ያልተማከለ (አሳታፊ) ፣ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ያተኮረ ፣ የእሴት ሰንሰለትን የተከተለ ፣ ስልታዊና መሰረታዊ ግቦችን ያካተተ (ሥርዓተ ጸታን ፣ ሥርዓተ ምግብን ፣ የአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ግብርናን (CSA) እና የስራ ዕድል ፈጠራ) እና ዘላቂነት ናቸው፡፡

በፕሮግራሙ የበጀት ድጋፍ በክፍል አንድ ከተሰሩ ዋና ዋና ሰራዎች መካከል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ፣ አሰራሮችን እና ክህሎትን በማሻሻል የግብርና አገልግሎት ጥራትን፣ አስፈላጊነት እና ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም የምግብ ሥርዓትን የመቋቋም አቅምን ለማሻሻል በቁጥር 79 የአ/አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን በቁሳቁስ እና በዙሪያ አጥር እንዲሁም በብሎክ ጥገና ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።

በተመረጡ የእሴት ሰንሰለት ምርቶችና በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በ316 አ/አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት እና በ3,647 አ/አደር ማሳ ላይ ሰርቶ ማሳያዎችን በማካሄድ ምርታማነትን ማሳድግ እና 19,288 አ/አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ወንደወሰን።

ይህንንም አሰራር እንደ ተሞክሮ በመውሰድ 11,982 አ/አደሮች በራሳቸው ማሳ ላይ ተግባራዊ ማድረግ መቻላቸው ጨምረው ገልጸዋል ፡፡

የአፈር ለምነት እና ጤናን ለማሻሻል በ15ቱም የፕሮግራም ወረዳዎች ላይ አበእያንዳንዱ አንድ የአነስተኛ ደረጃ የቨርሚ ካልቸር ማሰልጠኛ እና የሰርቶ ማሳያ ማዕከል በማቋቋም ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማትንና ጤናን ለማሳደግ 12 ኩሬዎችን በመገንባት 29,060 የተሻሻሉ የዓሳ ጫጩቶችን በኩሬ ውስጥ ማስገባት መቻሉን፤

የክልሉን የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ፣ የ15 ፕሮግራም ወረዳዎች የእንሣት ጤና ክልኒክ እና ጤና ኬላዎችን በቁሳቁስ በመደገፍ እና በጥቅል 28 የእንስሳት ማዳቀያ ቁሳቁስ በማቅረብና ስልጠና በመስጠት መጠናከሩን አንስተዋል።

18 የህክምናና የማዳቀያ በረት በማስራትና ሆርሞን እና የፆታ ለይቶ ማስወለጃ በማቅረብ ለ 666,750 የቁም እንስሳት የህክምና ፣ ለ984,189 የቁም እንሰሳት የክትባት እና ለ 215,052 የቁም እንስሳት የርጭት የአገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል ።

ከተዳቀሉት 5,939 የወተት ላሞች ውስጥ 3,441 አርግዘው 1,459 የተሻሻሉ ጥጆችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን በድጋፉ 86,758 አ/አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

የመስኖ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ለግብርና እና ለገጠር አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑና የግብርና መስኖ ውሃን ደህንነት ለማስጠበቅ በቁጥር 12 የተለያየ አይነት የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ 595 ሄክታር መሬት በማልማት 1,077 የቤተሰብ መሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት::

በመስኖ አውታሮችና ቴክኖሎጂዎች የተጠቀሙ አ/አደሮች 26,533.5 ኩንታል የተለያዩ የሰብልና የአትክልት ምርት በማምረት 71,890,000 ብር ገቢ ማግኘት መቻላቸውን አንስተዋል፡፡

የኢንተርፕራይዞችን ዕድገት በተመረጡ የእሴት ሰንሰለቶች ላይ በማስተዋወቅ፣ የግብርና ግብዓትና የምርት ገበያን ውጤታማነት በማሻሻል እና አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች የገበያ ዝንባሌን በማስተዋወቅ የገጠር ስልታዊ የግብርና ምርቶችን እና የገጠር የስራ እድሎችን ለማሳደግ እና የንግድ ማቀላጠፍ አገልግሎትን ለማሳደግ ፣ የምግብ እና የስነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ 123 አባላት ያሉት በቁጥር 14 ኢንተርፕራይዞችን በግብርና የንግድ ስራ በማደራጀትና በማሰማራት 2,036,990 ብር ገቢ ማግኘት እንዲችሉ መደረጉን አብራርተዋል፡፡


በቁጥር 7 የተለያዩ ዘመናዊ የግብይት ማዕከላትን፦ 2 የሰብል፣3 የቁም እንሰሳት እና 2 የአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ማዕከላት ግንባታ በማጠናቀቅ 139,494 ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

በተገነቡ የእንስሳት ግብይት ማዕከላት በቁጥር 47,588 የቁም እንስሳት ግብይት በመካሄዱ ለመንግስት 2,039,000 ብር ገቢ ማስገኘት መቻሉን አቶ ወንድወሰን ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ 240 ቶን የሰብል ግብይት ተካሂዶ ለመንግስት 288,000 ገቢ አስገኝቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥር 5 አነስተኛ ድልድይ በመገንባት 58,916 የህብረተሰብ ክፎሎች እንዲጠቀሙ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ለመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር በቁጥር አንድ መጋዘን እና በቁጥር አንድ የዘር ማቆያ ማዕከል በመገንባት ማህበራትን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ፣ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም ለስራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *