




የቤንች ሸኮ ዞን ትራንስፖርት መንገድ ልማት መምሪያ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በዘርፉ የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረም ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።
በግምገማው መድረክ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የዞኑ የንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉበላ እንደተናገሩት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ የሚነሱትን ችግሮችን በጥልቀት መፈተሽ ይገባል ብለዋል።
ትራንስፖርትና መንገድ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አውስተዋል።
አክለውም ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰሩ እንደሚገባቸዉ ገልፅዋል ።
በተያዘው በጀት ዓመት በትራንስፖርት ዘርፍ እየታየ ያለውን ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማጠናከር መረባረብ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ አበበ ኑራ የዞኑ ትራንስፖርት መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ ናቸው።
አቶ አበበ አያይዘው በየወቅቱ እየጨመረ ያለውን የህዝብ ፍላጎት ከአቅርቦትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ለማመጣጠን የሚያስችል የዘመነ የትራንስፖርትና የመንገድ አገልግሎት ለመስጠት የሚነሱ ችግሮች ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል ትራንስፖርት ዘርፍ አንዱ በመሆኑ በየደረጃ ያለው የዘርፉ ባለሙያዎች ላይ ግምገማ በማድረግ ሪፎርም እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ትርፍ እና ታሪፍን አለመቆጣጠር ፣ የስምሪት አሰጣጥ ፣ የተሽከርካሪ ብቃት ምርመራና መሰል ችግሮችን እርምጃ ወስደው ማስተካከል ከመድረኩ እንደሚጠበቅ አቶ አበበ ተናግረዋል።
ብልሹ አሰራርና የስነምግባር ችግሮች እንዳይከሰት በየደረጃ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና ተያያዥ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ አካላት ሂስ ግለሂስ እንደሚደረግ ከመድረኩ ተገልጿል
የግምገማ መድረኩ በትራንስፖርት ህግና ደንብ የሚመራ፣ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ተገቢውን አክብሮት የሚያሳይና አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የተሟላ ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሰ የትራንስፖርት ዘርፍ እንዲፈጠር እገዛ በማድረግ በዘርፉ የሚደርሰውን አደጋና ብልሹ አሰራር መቀነስ እንደሆነም ተገልጿል።
በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረም የተዘጋጀ ሰነድ በዝርዝር ቀርቦ በተሳታፊዎች ሐሳብ አስተያየት ተሰጥቶ ውይይት ተደርጎበታል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
