




በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መከፈቱ፣ አገልግሎት ፈላጊዎችን ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ ሲዳርግ የነበረውን ጉዞ እንደሚያስቀር የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጀማል ደስታው ገለጹ።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ መደበኛ አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩን አቶ ጀማል ጠቁመው ዜጎች የፓስፖርትና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግ ተቋሙ በሰፊው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጀማል ገለጻ፣ ተቋሙ ሀገራዊና ተቋማዊ ለውጡን ተከተሎ 11 የሪፎርም አጀንዳዎችን ቀርጾ ወደ ተግባር ገብቷል።
ከእነዚህም መካከል “የአገልግሎት አሰጣጥ” አንዱ ሲሆን፣ አሠራርን በቴክኖሎጂ የማዘመንና ተደራሽነትን የማስፋት ጉዳይ ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል።
በሪፎርሙ የመጡ ዋና ዋና ለውጦች መካከልም
የፓስፖርት የአገልግሎት ዘመን፡ ቀደም ሲል ለ5 ዓመታት ብቻ ያገለግል የነበረው ፓስፖርት፣ አሁን በሚሰጠው ኢ-ፓስፖርት (E-Passport) ወደ 10 ዓመት ከፍ እንዲል ተደርጓል።
አዲሱ ኢ-ፓስፖርት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አስተማማኝ የደህንነት መጠበቂያዎችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል።
ተቋሙ ቀደም ሲል በአዲስ አበባና በ12 ነባር ቅርንጫፎች ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማስፋት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሎች 11 እንዲሁም በአዲስ አበባ 4 (በድምሩ 15) አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ የተከፈተው ይህ ቅርንጫፍ፣ ነዋሪዎች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ጅማ ፣አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ረጅም ኪሎ ሜትር ጉዞ ያስቀራል።
ይህም የዜጎችን የጊዜ ብክነት ፣ ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ በማድረግ ህገ-ወጥ አሠራሮችን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አዲስ ፓስፖርት ማውጣት፣ የጊዜ ገደቡ ያለፈበትን ፓስፖርት ማደስ፤ የጠፋ ፓስፖርት ምትክ ማውጣት፤ የፓስፖርት መረጃ እርማት አገልግሎቶች ይሰጣል ሲሉ አቶ ጀማል ጠቁመዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በተመሳሳይ ሰዓት ሲስተሙ ለ5 ሰዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።
ላለፉት ሁለት ወራት የቀጠሮ ማስያዝ ሥራ ሲከናወን የቆየ ሲሆን፣ ከየካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በይፋ ሥራ እንደሚጀመር የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
