

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካለት ገለጻና የገንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ግንቦት 21 ቀን 2016 በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ ከጠዋቱ መክፈቻ መርኃ ግብር በኋላ በነበረው ሂደት ተሳታፊዎች በየህብረተሰብ ክፍላቸው በቡድን በመሆን ከወከሉት ማህበረሰብ ያመጧቸው የአጀንዳ ኃሳቦች ላይ ውይይት እያደረጉ ሲሆን ይህም ዛሬ ይጠናቀቃል።
በሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የኛ የሚሉትንና የተስማሙባቸውን የአጀንዳ ኃሳቦች በማጠናከር ለኮሚሽኑ በቃለ-ጉባኤ ተፈራርመው እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።
ያቀረቧቸው የአጀንዳ ሃሳቦች በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖሩ መድረኮች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይንፀባረቃሉ ተብሏል።
ተሰብሳቢዎች በቀጣዮቹ የምክክር ምዕራፎች ላይ የሚወክሏቸውን 121 ተወካዮች በመምረጥ ለሚቀጥሉት የምክክር ምዕራፎች እንደሚዘጋጁም ተጠቁሟል።
በመሆኑም እየተካሄደ ባለው የባለድርሻ አካላት መድረክ እስካሁን ያለው የምክክር ሂደት ላይ ገለጻ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ምክክሩ እስካሁን የመጣበትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንስተዋል።
አጀንዳ ማሰባሰብ ከታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ጀምሮ አካታች በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት በጋራ በሚኖራቸው ምክክር ለአጀንዳ ስብሰባው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የምክክር ምዕራፉ በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ የአራት ባለድርሻ አካላት ተወካዮችን በማሳተፍ እየተከናወነ እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር መሰረታዊ በሆኑ አገራዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ መሪዎች ልዩነታቸውን በመግባባት እንዲፈቱ እድል በመፍጠር ትልቅ ፋይዳ አለው።
ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ጠንካራና ቅቡልነት ላለው አገረ መንግሥት ግንባታ መደላድል መፍጠርም ሌላው የምክክሩ ዓላማ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
