


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሀገራዊ የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል ።
ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ቆየት ያሉ ያልተፈቱና በጋራ ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጡ መፍትሔዎችን ማግኘት የሚያስችለን መድረክ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
አስተያየት ከሰጡን መካከል ከቤንች ሸኮ የመጡት አቶ ሻንቆ ጋኪናንስ ምክክሩ የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት የሚያስችለንን ውጤት ያመጣል ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
ሌላኛዉኛው አስተያየት የሰጡን ከካፋ ዞን ጎባ ወረዳ የመጡት መላከ ሳህል ሀብታሙ ሀይሌ በበኩላቸው ማህበረሰብ መሪዎችን በመወከል በውይይቱ የተሳተፉ ሲሆን ምክክሩ እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት እጅግ ያግዛል ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት ከሸኮ ወረዳ አቶ እጅጉ ጺዳ የማህበረሰቡን ያልተፈቱ ችግሮችን ለመወያየት ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
አቶ ማጁር መኩሪያ በዳውሮ ዞን የጀግኖች አርበኞች ማህበርን በመወከል በውይይቱ እየተሳተፉ ሲሆን ውይይቱ ጥንት የነበረውን ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናት ይጠቅማል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመቻቻል የውጭ ጠላትን ለመመከት በአንድነት እናደርገው የነበረውን አንድነትና አብሮነት ዛሬም በመቻቻልና ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመመካከር እና በመፍታት ለትውልዱ አንዲት ኢትዮጵያን ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል ።
መምህራንን በመከልም ተሳታፊ የሆኑት መ/ር መላኩ ኡቴ በሰጡት አስተያየት የምክክር መድረኩ መመቻቸቱ ችግሮቻችንን በመመካከር ለመፍታት ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
በምክክር መድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት በምክክር መድረኩ ግለሰባዊ ከሆነ አጀንዳ በመውጣት ሊያግባቡ በሚችሉና የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ አጀንዳዎችን ማንሳት ይገባናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዛሬ በተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የውይይት መድረክ ለተሳታፊዎች አጭር ማብራሪ የተሰጠ ሲሆን መስማት ለተሳናቸው ተሳታፊዎች በአስተርጓሚዎች ገለጻ በማድረግና ቃለ መሀላ በመፈጸም ወደ ቡድን ውይይት ተሳታፊዎች አቅንተዋል።
በታጠቅ አበበ
