



የሚዛን አማን አይሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአይሮፕላን ማረፊያው ፕሮጀክት ጨምሮ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ተመልክተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ በመገንባት ላይ የሚገኘው ኤርፖርቱ በ252 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
ዞኑ ይዞታውን ከባለቤትነት ነጻ በማድረግ ሥራው እንዲቀላጠፍ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ልማት የጎላ ፋይዳ ስላለው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የአካባቢው ሥነ ምህዳር ለቱሪዝም ኢኮኖሚ ያለውን አቅም በመረዳትም ለቱሪስት መዳረሻ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ለአይሮፕላን ማረፊያው የመሬት ይዞታ ከይገባኛል ነጻ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱን በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ለ24 ሰዓት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶችም በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
