




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ከዞንና ወረዳ ለተውጣጡ የእንስሳት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የእንስሳት ጤና ፓኬጅ ስልጠና እና ክልላዊ የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሚሰጠውን የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር እና አሁን ባለው ሀገራዊና ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታ መነሻ የእንስሳት ጤና አገልግሎት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል በዘርፉ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር እና ለተሻለ ውጤት በጋራ ለመንቀሳቀስ ያለመ ነው ተብሏል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታመነ በቀለ እንደተናገሩት፣በክልሉ የእንሰሳት ሀብት ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ የበሽታ መከላከል ግንዛቤ ማሳደግ እና በክትባት ተደራሽነት ላይ በአጽንኦት መስራት ይገባል።
የተጀመረውን የእንሰሳት ሀብት ልማት ለማሳደግ የእንሰሳት ጤና በክትባት ላይ የተንጠለጠለ ብቻ መሆን የለበትም ያሉት ሀላፊው ለእንስሳት ጤና መሻሻል የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ትግበራ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ መበሰሩን ተናግረዋል።
በቢሮው የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ አለማየሁ በበኩላቸዉ፣ከዚህን በፊት የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ በእንስሳት ጤና አገልግሎት ላይ መሠረት ተደርጎ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ግን የእንሰሳት ምርታማነትን በተሻለ መልኩ ለማላቅ የሚረዳ የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ትግበራ ስርአት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ በገጠርም ሆነ በከተማ በእንስሳት ሀብት ልማት የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው በዚህ ልክ ውጤታማ ለመሆን እንዲቻል በጤና መከላከል ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመድረኩም የክልሉ እንሰሳት መድሃኒት ተዘዋዋሪ ፈንድ እና የእንሰሳት ጤና አገልግሎት የከፊል ወጪ መጋራት የእስካሁን አተገባበር ዙሪያ የተደረገ የመስክ ዳሰሳ ጥናት እና በእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ትግበራ ስርአትን በተመለከተ ዉይይት ተደርጓል፡፡
አንዳንድ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ስርዓቱ በክልሉ የተጀመረዉን የእንሰሳት ሀብት ምርታማነት ለማላቅ የሚያግዝ ስለሆነ ለተፈጻሚነቱም የሚጠበቅባቸዉን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸዉን ተናግረዋል፡፡
በካሳሁን አሰፋ
