




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ከክልሉ ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከካልም እና ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የግብርና ፕሮግራሞች ትግበራ፣ በሥነ ምግባር ግንባታና ብልሹ አሠራር መከላከል ዙሪያ ለተጠሪ ተቋማትና ማዕከላት፣ የዞን እና የወረዳ ግብርና ጽ/ቤቶች የሥነ ምግባር ፎካሎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ይገኛል፡፡
በስልጠናው መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ግብርና ከሴክተር በላይ መሆኑን አንስተው ሴክተሩ ለሙስና አደጋዎች በጣም የተጋለጠ በመሆኑ ለሥነ ምግባር ፎካሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት እና የሥነ ምግበር ተቋማት መገንባት ተልዕኮውን የሚገልፅ እና በዓላማ እንድሰራ ህጋዊ መሠረት የሚጥል መሆኑን
ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሙስናን የሚቃወም ተቋማዊ በህል በመገንባት ሂደት ውስጥ የሥነ ምግባር ፎካሎች ሚናቸው የማይተካ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽነር ሙሉሰው አክለውም ሰልጣኞች በግብርናው ዘርፍ የስነ ምግባር ልህቀት አንድ እርምጃ ወደፊት ለማላቅ በየተቋማቱ የሥነ ምግባር አምባሳደር፣ አርአያ እና የለውጥ አራማጅ በመሆን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር አቶ ገዛኸኝ አለማየሁ የግብርና ስራ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሰፊ የሆነ የልማት ስራዎች፣ ሀብት የሚመደብለት እና ብዙ ፕሮጀክቶችን በመያዝ ተግባራት የሚከናወኑ መሆኑን አንስተው ይህንን ስራ ለማሳለጥ ለግብርና ቢሮ ተጠሪ ለሆኑ ለ4 ተጠሪ ተቋማት፣ለ6ቱም ዞኖች እና ለ4ቱም ማዕከላት የስነ ምግባር ፎካሎችን የመመደብ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ለሥነምግበር ግንባታና ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የሥነ ምግበር ፎካሎች ግንዛቤ ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑን ይህ ስልጠና መዘጋጀቱን ተናግረዋል ፡፡
በግብርና ዘርፍ በየግዜው የሚወርደው ሀብት ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በአግባቡ ጥቅም እንዲሰጥ በየጊዜው የመከተተል፣ ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል እና የተሳሳቱ ድርጊቶችን ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነትን እንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የስነምግባር ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ታደሰ አይበራ ሥነ ምግባር ምንነት በሚል የስልጠና ሰነድ የቀረበ ሲሆን በሌሎችም አካላት ለስልጠና የተዘጋጁ ሰነዶች ቀጥሎ እንቀረበ ይገኛል፡፡
ስልጠናው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ60 የሚበልጡ የግብርና ቢሮ ተጠሪ ተቋማትና ማዕከላት፣ የዞን እና የወረዳ ግብርና ጽ/ቤቶች የሥነ ምግባር ፎካሎች እየተሳተፉ ነው ፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
