




ማዕከሉ ዳግም መከፈቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በነጋዴዎች ላይ ይደርስ የነበረዉን ጫና የሚቀነስ ነዉ ስል የካፋ ዞን ቡና አቅራቢዎች እና አዘጋጆች ማህበር ገልጿል።
የካፋ ዞን ግብርና፣ ደን፣ አከባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ ልማት መምሪያ ኃላፊና የቦንጋ ምርት ጥራት ምርመራና ሴርተፊኬሽን ማዕከል አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋዎ አባመጫ ቡና ለዞኑ ማህበረሰብ ከባህላዊና ታሪካዊ ቁርኝት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዉ የጎላ ነዉ ብለዋል።
በዚህም የምርት ጥራት ቁጥጥር ማዕከሉ በቦንጋ ተቋቁሞ አገልግሎት እየተሰጠ የቆየ ቢሆንም ወደ ተለያዩ ማዕከላት በመከፋፈሉ በተፈጠረዉ እንግልት ምክንያት ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከየተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ማዕከሉን ለማቋቋም ተችሏል ብለዋል።
ኃላፊው ይህ ስራ የጀመረዉ ማዕከልም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካፋ፣ ቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞኖችን እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል ማዣንግ ዞንና አካባቢዉ ያለውን የቡና ምርት ይዞ የሚሰራ የግብይት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋሙ መቋቋም ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ዕድል ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለዉ ያብራሩት አቶ ጋዎ የአካባቢው ወጣቶችም ተገቢ ካልሆኑ አስተሳሰቦች በመላቀቅ የመጣውን ዕድል ልጠቀሙ እንደሚገባም አሳስቧል።
ማዕከሉን በይፋ ስራ እንድጀምር የካፋ ዞን አስተዳደርን ጨምሮ አስተዋፅኦ ላበረከቱት አካላት የመምሪያዉ ኃላፊና የአብይ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ አቶ ጋዎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የማዕከሉን ሥራ መጀመርና ሌሎች ከግብይት ማዕከሉ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ በቀጣይ የቡና ልማትና ግብይት ሥራ ላይ ተሣታፊ አካላት፣ የፌደራል የክልልና የዞን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ እንደሚኖርም አቶ ጋዎ ገልፀዋል።
እንደሁም ማዕከሉ በዋናነት ቀጥታ ትስስር ላይ እንደሚሰራ የቦንጋ ምርት ጥራት ምርመራና ሴርተፊኬሽን ማዕከል ኃላፊ አቶ ያስን አባጊሳ ተናግረዋል።
ማዕከሉ በቦንጋ ከተማ በመከፈቱ ከዚህ በፊት በነጋዴው ማህበረተሰብ ላይ ይደርስ የነበረውን መስተጓጎልና እንግልት በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልጸው፣ የከተማዉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል።
ከዚህም ባለፈ ለበርካታ ስራ አጦች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የገለፁት የማዕከሉ ኃላፊ፣ በቡና ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ላኪዎችና አቅራቢ ድርጅቶች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ማዕከል በመሆኑ ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።
የካፋ ዞን ቡና አቅራቢዎች እና አዘጋጆች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ለማ ማሞ በበኩላቸው፣ የቦንጋ ምርት ጥራት ምርመራና ሴርተፊኬሽን ማዕከል ስራ መጀመሩ ከዚህ በፊት በወረፋ መጨናነቅና ረጅም ኪሎ ሜትር በመጓዝ በነጋዴዎች እና አቅራቢዎች ላይ ይደርስ የነበረውን መጉላላት እንዲሁም ተጨማሪ ወጪ እንደሚያድንም ተናግረዋል ሲል ደሬቴድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
