









የሸኮ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቲካሻ ቤንጊ ” በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ተከብሯል ።
በበዓሉ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ቲካሻ ቤንጊ የመተሳሰብና የአንድነት በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የሸኮ ብሔረሰብ በዓሉን ሲያከብር ይበልጥ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጠናከር የሚያስችል ታሪክና ባህል እንዲጎለብት የሚያስችል ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
አካባቢው የሰብል ምርት፣የማር ምርት፣የቡና ምርት በስፋት የሚገኝበት በመሆኑ የአካባቢው ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲያንሰራራ በተገቢው ማልማት ይገባልም ብለዋል።
የህዝብ ባህሎች የአንድነትና የመተሳሰብ እሴት ያሏቸው በመሆኑ ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባም በዕለቱ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ የሸኮ ብሔር ያለውን አካፍሎ በጋራ ማዕድ የሚቃመስበት ለተፈጥሮ ጥበቃ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ህዝብ ነው ብለዋል።
ቲኬሻ ቤንጊ የተጣሉ የሚታረቁበት ህዝቡ ለሰላም ያለውን ትልቅ ቦታ ማሳያ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ባህላዊ እሴት ያለው በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ለረጂም ዓመታት ባለመከበሩ የታሪክ መሸራረፍ እንደገጠመውና ይህንን የታሪክ መሸራረፍ ለመቅረፍ አሁን ላይ የተጀመረው ስራ ለትውልዱ እንዲተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ፍቅሬ አማን በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክትም የብልጽግና ፓርቲ የህዝቦች በህልና ታሪክ በተገቢው እንዲለማ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
የሸኮ ብሔር ዘመን መለወጫ ቲካሻ ቤንጊ ሰላም ፣አንድነትና አብሮነት ይበልጥ በአካባቢው እንዲበለጽግ የሚያስችል መሆኑንም አቶ ፍቅሬ አማን ተናግረዋል ።
የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጸጋዬ ማሞ አካባቢው በኢኮኖሚ የበለጸገ እንዲሆን ያሉንን ጸጋዎች በተገቢው ማልማት ይገባል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በዕለቱም ባስተላለፉት መልዕክት የሸኮ ብሔር ዘመን መለወጫ ቲካሻ ቤንጊ የአብሮነት፣የመተሳሰብ ፣የአንድነትና የሰላም እሴት ያለው ባህላዊ በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋለ።
ቲካሻ ቤንጊ ጠንካራ የህዝብ እና መንግስት ግንኙነቶችን የሚፈጥር የልማት ስራዎችን የሚያሳልጥ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል ።
የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉሩሙ የሸኮ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቲካሻ “ቤንጊ በብሔረሰቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና በባህላዊ ክዋኔዎች ከሚከበሩት በዓላት ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል ።
በአካባቢው የደረሱ ሰብሎች፣ፍራፍሬዎች፣የማር ምርት እንደደረሰ ተሰብስቦ ህብረተሰቡ በጋራ በየጎሳቸው ማዕድ የሚቃመሱበት ለቀጣይ አዝመራ የሚመራረቁበትና ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት በዓል መሆኑንም አቶ አሪ ተናግረዋል ።
በዓሉ ከጥር 8/2017 ዓ/ም ጀምሮ በዓሉ በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች መከበሩንና የዛሬው የፍጻሜ በዓል መሆኑን ተናግረዋል ።
ቲኬሻ ቤንጊ ከክልሉ የተለያዩ የመንግስት አካላት፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣ጎሳ መሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በድምቀት በሸኮ ከተማ ተከብሯል ።
በታጠቅ አበበ
