










በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ካፋ ዞን፣ ጊምቦ ወረዳ፣ ሾምባ ኪጭብ ቀበሌ የተከሰተውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ለመፍታት ያለመ ህዝባዊ ውይይት በቀበሌው ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዲሁም የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ከሌሎች የክልል እና የካፋ ዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከአከባቢው ከተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ወይይት አድርገዋል።
በቀበሌው የአንድ ግለሰብ መገደልን ተከትሎ የተፈጠረው ዉጥረት ተከትሎ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን በዚህም በቀጠናው ወቅታዊ የሠላም መደፍረስና የፀጥታ ስጋት መፈጠሩ ተጠቁሟል።
የክልሉ መንግሥት በተከሰተው አሳዛኝ ድርጊት በደረሰው ጉዳት ማዘኑና በቀጠናው የተከሰተውን የፀጥታ ስጋት በዘላቂነት በመፍታት አከባቢውን ወደ ሚታወቅበት የቀደመ ሠላምና ደህንነት ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑ ተገልጿል።
አከባቢው ለረዥም ዓመታት በህብረብሔራዊ ወንድማማችነትና በልማት እንዲሁም በጠንካራ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን የአብሮነት ዕሴት የሚሸረሽርና በህዝቦች መካከል እርስበርስ መጠራጠር የሚፈጥር ምልክት እየተስተዋለ መሆኑ ተነግሯል።
ቀጠናው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ክምችት እየጨመረ መመጣቱንና በዚህም ግለሰቦች ወንጀል ፈጽመው ስገኙ በብሄር ጉያ በመሸሸግ ግጭት ለማስፋት የሚደረግ ህገወጥ ድርጊት መኖሩ ነው የተመላከተው።
አጥፊዎችን በህግ በማስጠየቅ አከባቢውን ወደ ሚታወቅበት የቀደመ ሠላም መመለስ፤ የጦር መሳሪያ ዝውውር መቆጣጠር እና ህዝባዊ ውይይቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሠላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ ነው በመድረኩ የገለጸው።
ግጭት እንዳይከሰትና የተፈጠረዉ ዉጥረት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም የፀጥታ መዋቅር ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት የተገለጸ ሲሆን የዞኑ መንግሥት በየደረጃው ህዝባዊ የሠላም ውይይት መድረኮች በመፈጠር ዘላቂ ሠላምን ማስፈን እንደሚገባ ተገልጿል።
ሁሉም ለሠላም ዝግጁ በመሆን እርቀ ሠላም ማድረግ እንደሚገባ ያነሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች የአብሮነት ማህበራዊ ዕሴትን የሚሸረሽር እና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ትንኮሳዎች መቆም እንዳለበት ጠይቀዋል።
የተፈጠረውን ክስተት በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ባልተገባ መልኩ የብሄር መልክ እንዲይዝ በማድረግ የአከባቢውን ገጽታ ለማበላሸት እንዲሁም ተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ተግተው የሚሰሩ አካላት ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የተጠየቀ ሲሆን የክልሉ መንግሥት በበኩሉ የችግሩን መንስኤ በማጥራት በወንጀል ተግባሩ የተሰማሩትን በህግ አግባብ የማስጠየቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝ ከህግ አግባብ ውጪ የሚወሰድ የደቦ ፍርድ ህገወጥ ከመሆኑ በላይ ተጨማሪ ግጭት የሚፈጠር በመሆኑ ሠላም ወዳዱ ህዝብ ድርጊቱን በጽኑ በማውገዝ የተከሰተው ችግር በውይይትና በህግ አግባብ ብቻ መፈታት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በቀጠናው የጽንፈኛ አጀንዳ አራማጅ በመሆን በህዝቦች መካከል ፀብ የሚዘሩ ግለሰቦችን በህግ የማስጠየቁ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የመሳሪያ መፍታት እንዲሁም የፀጥታ መዋቅር በመፈተሽ ተጠያቂነት የማስፈን ስራ እንደሚሰራ ተጠቅሟል።
የካፋ ዞን እንዲሁም የጊምቦ ወረዳ መዋቅር ችግሩ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መሰል ህዝባዊ ውይይት በማድረግ የሠላምና እርቅ ኮንፈረንስ በማድረግ ሠላምን እንዲያጸናም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዕድገቱ በዛብህ
