







መንግሥት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን በመስራት በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።
ይህ አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ዘላቂነትን በመደገፍ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማእቀፍ ለመመሥረት የሚያስችል ነው። የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ፈጠራን የሚያበረታታና ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል። የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን የሚያጠናክርና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደጊያ እንደሚሆንም ተመልክቷል ።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለትን መፍታት፣ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፣ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶትን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል በመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ማጠናከርና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ቁልፍ ተግባራት ናቸው፡፡
በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርምን ተከትሎ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ገልፀዋል፡፡
አንድ ሀገር ጠንካራ ኢኮኖሚ ገነባ የሚባለው ተከታታይነት ያለው የምርት እድገት ሲኖር፣ ገበያን መሰረት ያደረገ የገንዘብ አቅርቦት ሲኖር፣ የስራ አጥ ቁጥርን በየጊዜው እየቀነሱ መሄድ፣ የዋጋ ንረትን መቀነስና እዳን መቀነስ ሲቻል መሆኑን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው የሀገራችን የምርት ዕድገት እየጨመረና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገራችን የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የተወሰደው ትልቁ እርምጃ የገንዘብ ፖሊሲና የምንዛሬ ማሻሻያ በመሆኑ ፖሊሲውን በተገቢው መረዳት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ተመስገን የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ገበያው ላይ ሰው ሰራሽ የገበያ ዋጋ አለመረጋጋት እንዳይፈጥር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ከሰሞኑ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ቀድሞ በገቡ ምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪና የምርት መደበቅ መስተዋሉን ያነሱት አቶ ተመስገን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ጠንካራና ታማኝ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የንግድ አሻጥር የሚያደርጉ ነጋዴዎች ምርት እንደሌለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩት ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በክልሉ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም በፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በርካታ የክልሉን ዜጎች የሚጎዳ ተግባር እየፈፀሙ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
ክልሉን እየጎዳ ያለው ያለአግባብ ዋጋ መጨመር፣ ምርት የመደበቅ እና ምርት የማሸሽ ጉዳይ ነው ያሉት የቢሮው ኃላፊ ለዚህም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ለክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ በአዋጅ የተሰጣ ስልጣን መኖሩንና እርምጃ አወሳሰዱ የራሱ ገደብ መኖሩን ገልፀዋል፡፡
የሸማቾች መብት ማስከበር አዋጅ ቁጥር 813/2006 እና አዋጅ ቁጥር 1243 የንግድ አዋጅ መኖሩንና እነዚህ አዋጆች የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቁ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን በክልሉ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪና ምርት በሚደብቁ የንግድ ሱቆቻቸውን የማሸግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡በዚህም በክልሉ ባልተገባ ሁኔታ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ በአጠቃላይ 451 ሱቆች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
ለ84 የንግድ ድርጅቶች ማስጠንቃቂያ መሰጠቱን የገለጹት አቶ ተመስገን በምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ በመጨመር እና ምርት በመደበቅና በማሸሽ ከፍተኛ የሆነ የምርት እጠረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ 12 ነጋዴዎችን ከህግ ጋር በማገናኘት ምርመራ ተጣርቶ ለአቃቤ ህግ መተላለፉን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በሆቴል፣ በምግብ እና መጠጥ ቤቶችም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ ነው ያሉት ኃላፊው ድርጊቱም ከማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የማይገናኝ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከክልሉ ጀምሮ በየደረጃው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት የቢሮው ኃላፊው በክልሉ የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ሱቆቻቸው ከማሸግ ባለፈ ህገዊ እርምጃ የመውሰድ እና የንግድ ፍቃድ የመቀማቱ ሥራዉን አጠናክሮ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል ።
የንግድ ተቋማት ሱቆቻቸውን የማሸግና ህጋዊና አስተዳዳራዊ እርምጃ መወሰዱ ጊዜያዊ መፍትሔ ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን በዘላቂ መፍትሔ እንዲሆን መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት በራሱ ዶላር በጅቶ የሚያስገባው የፍጆታ ምርቶች መኖሩንና ከዚህ በፊት የፍጆታ ምርቶችን የሚያሰራጩ ማህበራትንና ስኳርና ዘይት አቅራቢ ተመኘ ባለሀብቶችን በመመልመል ምርቶቹን ወደክልሉ ማዕከል እንዲያስገቡ መላካቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ በግብርና ምርቶች ላይ ያን ያህል የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን የገለጹት አቶ ተመስገን የማሻሻያ ከመደረጉ በፊት መንግሥት የምርት እጥረት እንዳይከሰት ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕረግራም ቀርጾ በወተት፣ በዶሮና እንቁላል እንዲሁም በማር ምርት መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱንንና በክልላችን ተግባሩ በተደረጀ መንገድ በመፈፀም ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጂ ካለው ፍላጎት አንፃር አቅርቦትቱ አሁንም የማይመጣጠን በመሆኑ ለዚህም ምርት ካለበት ዞኖች የምርት እጥረት ወዳለው ዞኖች ምርቶችን በማሸጋገር ተጠቃሚው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብና ገበያን የማረጋጋት ስራ በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለዚህም በክልላችን በግብርና ምርት አምራችና አቅራቢ የሆኑ ማህበራት ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ ከኮሌጆች እና ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም አጎራባች ክልሎች ጋር የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ የቁጥጥር እና ድጋፍና ክትትል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም ቢሮው የሚያደርገውን የቁጥጥር፣ የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ የድጋፍ እና ክትትል ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ተመስገን ከበደ አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በክልሉ ያሉ የንግድ ተቋማትና አቅራቢ ነጋዴዎች በምርት ላይ ያልተገባ ዋጋ ከመጨመር እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት አቶ ተመስገን ከበደ ሸማቹ ማህበረሰብም ከወትሮ በተለየ መልኩ በምርት ላይ የተለየ የዋጋ ጭማሪ ሲያስተዉል ለህጋዊ አካላት ጥቆማ በማድረስ እንዲተባበር አሳስበዋል ።
