







ለሁለት ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲደረግ የነበረው ለሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ውይይት ተቋጭቷል።
“ከቃል እስከ ባህል ” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ለብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ሲያደርጉ የነበረው ውይይት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው ቀን ውይይት የብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ የክልሉ መንግስት ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ አብራርተዋል ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና ስነምግባር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ያዙ በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራትን የሚገልጽ ሪፖርት አቅርበዋል ።
በቀረቡት የመወያያ ሰነዶች ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየት እና የግንዛቤ ጥያቄዎች ተነስተው ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቷል።
በዚህም በብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጡ ስልጠናዎች መሠረታዊ ለውጦች የተገኙበትና የአስተሳሰብ አንድነት እንዲረጋገጥ ያደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ ገልጸዋል ።
ስልጠናውን ተከትሎም በክልሉ የጠራ አባል የማፍራት ጉዳይ ከአመራሩ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም አቶ ነጋ አሳስበዋል ።
በየአካባቢው ያሉ የመልማት ጸጋዎችን በመጠቀም አቅማችንን አሟጠን በመስራት ብልጽግናን ማረጋገጥ ከሁላችንም አመራሮች የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
ባለፉት ጊዜያት በኢኮኖሚው ፣በፖለቲካው ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተገኙ ለውጦችን የማስቀጠል ጉዳይ ከአመራሩ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ በብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ የተካተቱ አዳዲስ ሀሳቦች ምግባራችንን የሚገልጹ ስያሜዎችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ አስረድተዋል ።
እንደ ሀገር ብልጽግና ፓርቲ ለውጥን በሪፎርም መንገድ ተከትሎ መምጣቱን እና ሀገራዊ እጥፋቶችን እየፈታ በመምጣቱ መሠረታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል ።
የመጡ ለውጦች በብዛትና በፍጥነት፣በጥራት፣አለም አቀፋዊ ስታንዳርድን የተከተለና አካታች መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አመራሩ የብልጽግና ባህል እሳቤዎችን በመላበስ ሌላው ባህል እንዲያደርገው ያልተቀየሩ ፖለቲካዊ ባህሎቻችንን ማስወገድ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አመራሩ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን ተከትሎ በመስራት በክልሉም ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎችን ይበልጥ ማጠናከር ከአመራሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ አሳስበዋል ።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልል ከፍተኛ አመራሮች ለሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ውይይት በተነሱ ሀሳቦች ላይ የጋራ አረዳድ በመያዝ ተጠናቅቋል።
በታጠቅ አበበ
