
ኢትዮ ቴሌኮም የኮፐር መስመሮችን ወደ ፋይበር በመቀየር ዘመናዊ ባለገመድ ብሮድባንድ ኢንተርኔትና በዳታ ላይ የተመሰረተ የድምጽ አገልግሎት ለማቅረብ “ኮፐር ስዊች ኦፍ” የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ይፋ የሆነውን አገልግሎት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ከዚህ ቀደም የነበረው የኮፐር አገልግሎ በቴሌኮም ኢንዱስትሪው ከ150 ዓመታት በላይ ማገልገሉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ለ130 ዓመታት ለደንበኞች የባለገመድ መደበኛ ስልክና ላለፉት 20 ዓመታት ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ሲያገለግል ነበረ ብለዋል፡፡
“ኮፐር ስዊች ኦፍ” ኢኒሼቲቭ የባለገመድ የቴሌኮም አገልግሎት ደንበኞችን ከነባሩ የኮፐር መስመር የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ወደሚያስችለው የፋይበር መስመር ያለምንም ክፍያ በነጻ ለመቀየር ያስችላል ተብሏል፡፡
ኢኒሺየቲቩ በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ 60 ሺህ በክልል ከተሞች ደግሞ 40 ሺህ በአጠቃላይ 100 ሺህ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን÷ በመጀመሪያው ምዕራፍ የ31 ሺህ ደንበኞችን መስመር ለመቀየር እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የኮፐር ኔትወርክ በፋይበር በመተካት የ10 ሺህ ደንበኞችን አገልግሎት ወደ ፋይበር ኔትወርክ ለመቀየር እቅድ እንደተያዘም ተመላክቷል፡፡
በአዲሱ የፋይበር ኔትወርክ መስመር ደንበኞች አሰራራቸውን ለማቀላጠፍና ለማዘመን የሚጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች የሚፈልጉትን ፍጥነት በላቀ ሁኔታ ማሟላት ከማስቻል ባለፈ አሁን የተዘረጋው የፋይበር ኔትወርክ ሳይቀየር የደንበኛው ፍላጎት ሲያድግ አቅሙን ከ1 ጂ ወደ 10 ጂ ብሎም ወደ 50ጂ ለማሳደግ ያስችላል፡፡
እንዲሁም ለወሳኝ ተልዕኮ አገልግሎቶች እጅግ አስተማማኝ አገልግሎት ለማቅረብ እንደ ክላውድ እና ኤጅ ኮምፒውቲንግ፣ አይኦቲ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ኢንተርቴይንመንት፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ በርካታ ስማርት ሆም እና ሌሎችም የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ኮፐር ኔትወርክን በቀጣይ 3 አመታት፣ የክልል ዋና ዋና ከተሞችን ደግሞ በቀጣይ 5 ዓመታት እንዲሁም የዞን እና ወረዳ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ታቅዶ ትግበራ ተጀምሯል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡
