



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሱፐርቪዥን ቡድን በኮንታ ዞን በፓርቲና በመንግስት ስራዎች ላይ ለ15 ቀናት ባደረጉት የመስክ ምልከታ አፈፃፀም ላይ ከዞኑ ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
ሱፐርቪዥን ቡድኑ “የተቀናጀ ድጋፋዊ ክትትል ለውጤታማ ተግባር አፈፃፀም” በሚል መሪ ቃል በዞን ማዕከል፣ በኤላ ሀንቻኖ፣ በአመያ ዙሪያ እና በጪዳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ቀበሌዎች የመስክ ምልከታ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የዞኑን የመስክ ምልከታ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የሱፐርቪዥን ቡድን አስተባባሪና የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ ክልላችን ካለው እምቅ ተፈጥሮ ሀብት መነሻ ያለውን አቅም እንደየአካባቢዎች ያለውን ዕድልና ፀጋ በመጠቀም የብልፅግና ዓላማና የተቀመጡ ግቦችን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ፤ በኮንታ ዞን እየተሰሩ ያሉ የመንግስት እና የፓርቲ ተግባራት ውጤትና ተሞክሮ የተወሰደበት በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በተለይም በዞኑ በትምህርት፣ በፀጥታ፣ መሠረተ ልማትን በማስፋፋትና መሠል ዘርፎች ተምሳሌት የሚሆኑ ስራዎችን ተሰርተዋል ያሉት የሱፐርቪዥን ቡድን አስተባባሪው በግብርና ሜካናይዜሽንና ኩታ ገጠም እርሻ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የሚታየውን ውጤት አስፍቶ መሄድ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በቀጣይም ከማዳበሪያ ዕዳ አመላለስ፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ተሞክሮዎችን ማስፋት፣ የወጣቶችና ሴቶች ክንፍ ማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ በአጠቃላይ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች ትግበራ ማጠናከር ያሻል ያሉት አቶ ግዛው በዚህም የህብረተሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ በበለጠ በማሳደግ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሌሎች የክልሉ ሱፐርቪዥን ቡድን አባላት ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም የሚታዩ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው በኮንታ ዞን ደረጃ ባደረጉት ምልከታ ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋጠ መምጣቱን አስረድተዋል።
የተጀመሩ የፓርቲና የመንግስት ስራዎችን በትኩረት ማስቀጠልና የአካባቢውን እምቅ አቅም በመለየት ስጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፣ የመረጃ አደረጃጀት በማሻሻልና ተሞክሮዎችን በማስፋፋት መስራት ያሻልም ብለዋል።
የዞኑ ስራ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በበኩላቸው ዞኑ ከተደራጀ ወዲህ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ዘርፈ-ብዙ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
እየተተገበሩ ያሉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮችን ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር አስተሳስሮ በመምራት ላይ መሆናቸውን ያነሱት ስራ አስፈፃሚዎቹ በጥንካሬ የታዩትን የበለጠ ለማጠናከርና በጉድለት የታዩትን ከተሰጡ ግብረ-መልሶች መነሻ መላውን አመራርና ሕዝቡን በማስተባበር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ከዞን መንግስት አቅም በላይ በሆኑ የክልልና የፌደራል ፕሮጀክቶች፣ የፀጥታ ጉዳዮች፣ የመንገድ ካሣ እና መሠል የህዝብ ጥያቄዎች ላይ የክልልና የፌደራል መንግስት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የድጋፍ ቡድኑ በኮንታ ዞን ከፓርቲና ከመንግስት ተግባራት አንፃር ለክልሉም ተስፋ ሰጪ ስራዎች መኖራቸው የተናገሩ ሲሆን በጉድለት የታዩ ተግባራትን በማረም እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ መስራት እንደሚገባ መመልከቱን የዘገበዉ የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።
