በአቪዬሽን አሰራር ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ የተባለው ተጠርጣሪ “ዳዊት ድሪባ በዳኔ” በሚል ስም የ3 ጊዜ የሞት ፍርደኛ እንደነበር ፖሊስ አስታወቀ

Spread the love

ሰሞኑን በአቪዬሽን አሰራር ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ የተባለው ተጠርጣሪ፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ተከሶ “ዳዊት ድሪባ በዳኔ” በሚል ስም 3 ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት እንደነበር ፖሊስ ገልጿል፡፡

ከፖሊስ የምርመራ ማህደር ማረጋገጥ እንደተቻለው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ታሕሳስ 25 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዘረፋ፣ በቅሚያ፣ በሌብነት፣ በቤት ሰብሮ ስርቆት እና በደንብ መተላለፍ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪው ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ ፣ ጀማል ኑሩ እና ዳዊት ድሪባ በዳኔ የሚሉ ስሞችን በመጠቀም 11 የጦር መሣሪያ መዝረፍ ወንጀል፣ 6 ቅሚያ ወንጀል፣ 3 ሌብነት ወንጀሎች፣ 3 ሰው መግደል ወንጀል፣ 2 ስርቆትና ቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀሎች፣ አንድ ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል፣ ከእስር ማምለጥ ወንጀል እና አንድ ደንብ መተላለፍ የወንጀል ሪከርድ በአጠቃላይ 28 የወንጀል ሪከርዶች ያሉበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ከፖሊስ የምርመራ ማህደር እንዳረጋገጠው፤ ከዚህ ውስጥ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 24 ቀን በዋለው ችሎት 6 መዝገቦችን ሦስት ጊዜ አጣምሮ 3 ጊዜ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡

በድጋሚ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዚያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት በጦር መሣሪያ የታገዘ የዘረፋ፣ ከእስር ቤት የማምለጥና በሌብነት ወንጀል የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ያስተላለፈበት መሆኑ ነው ተገለጸው፡፡

ተጠርጣሪው በውሳኔው መሠረት ማረሚያ ቤት የገባው ይግባኝ ጠይቆ የሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ የተቀየረለት ቢሆንም፣ በድጋሚ ይግባኝ በማለቱ ቅጣቱ ወደ 25 ዓመት ተቀንሶለት ለ17 ዓመታት በማረሚያ ቤት ከቆየ በኋላ በይቅርታ መፈታቱን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ያለው ኢቢሲ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *