በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ባንክ ለመክፈት ዝግጅት ተጠናቀቀ

Spread the love

በቅርቡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ባንክ ለመክፈት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የዐይን ባንክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ÷ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በቅርቡ የሚከፈተው የዐይን ባንክ የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል፡፡

ባንኩን ለመክፈትም የቦታ ዝግጅት እና የግብዓት አቅርቦት መጠናቀቁን ጠቅሰው÷ በቅርቡ የሰው ኃይል በማሰልጠን ወደ ሥራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 155 የዐይን ብሌን ለማሰባሰብ ታቅዶ 203 የዐይን ብሌን መሰብሰብ መቻሉንም ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም 300 በጎ ፈቃደኞች የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ለማስገባት ታቅዶ 239 በጎ ፈቃደኞች ከሕልፈተ-ሕይወት በኋላ የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ለመሰብሰብ ከታቀደው 240 ሺህ 514 ዩኒት ደም 217 ሺህ 295 መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ ያለው የሕብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መሆኑን አመላክተው ለዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የዘንድሮው አፈጻጸም 28 ነጥብ 4 በመቶ ወይም በ48 ሺህ 7 ዩኒት ደም ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የተሰበሰበው ደም 99 ነጥብ 6 በመቶ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

አፈፃፀሙ እየተሻሻለ ያለ ቢሆንም የሕክምና ተቋማት የደም ፍላጎት እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ስላለ የደም እና ዐይን ብሌን ልገሳው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ያለው ኤፍኤም ሲ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *