በክልሉ የሚከናወኑ የፌደራል መንገድ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በመተባበር አዲስ ተሻሽለው በወጣው ካሳ አዋጅ ላይ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነዉ።

የስልጠናዉን መድረክ የከፈቱት በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሀገራዊ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ሥራአስፈጻሚ አቶ ተዎድሮስ ተገኝ እንዳሉት፣ መድረኩ አዲስ በተሻሽለው የካሳ አዋጅ፣ በክልሉ ለሚከናወኑ የፌዴራል መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲሁም በክልሉ የሚዘረጉ መሠረት ልማት ቅንጅት አፈጻጸም ዙሪያ የሚደረግ ነዉ።

አዲስ የተሻሻለው የካሳ አዋጅ በክልሉ የፌደራል ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ እየገጠመ ያለዉን ክፍተት የሚቀርፍ እንደሆነም ስረአስፈጻሚዉ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ፍትሃዊ የሆነ የመንገድ ስርጭት እንዲኖር በሰፊው እየተሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተያዘው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቅ በክልሉ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትና መዋቅሮች ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ሁሉም የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ቴዎድሮስ ተገኝ ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ ኢንጂነር ምትኩ በድሩ (ዶ/ር ) አዲስ የተሻሻለዉ የካሳ አዋጁ በክልላችን እየተገነቡ ለሚገኙ መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በቂ ግንዛቤ ለመያዝ የሚረዳ በመሆኑ ለተፈጻሚነት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት ።

በመድረኩ በክልሉ እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃና የክልሉን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች እና የካሳ ማሻሻያ አዋጅ ሰነድ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚደረግ ይሆናል።

የክልሉ ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም፣ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዞን አስተዳዳሪዎች፣የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳደር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመድረኩ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *