




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ ስራ የጀመረው “የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት” ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ለ17 ሺህ 800 ዜጎች አገልግሎት መስጠቱን የክልሉ መሶብ አንድ ማዕከል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስራት አዳሮ አስታወቁ።
ማዕከሉ የመንግስት አሰራርን በማዘመን ረገድ እያሳየ ስላለው ውጤት ማብራሪያ የሰጡት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በአሁኑ ወቅት በአንድ ማዕከል ውስጥ አምስት የክልልና አራት የፌዴራል ተቋማት ተቀናጅተው 35 የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አስራት እንደገለጹት፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩትን፦ያልተገባ እንግልትና የቢሮክራሲ ሰንሰለት፣ብልሹ አሰራርና ግልጽነት የጎደላቸው አሰራሮችን፣እንዲሁም የአገልግሎት ፈላጊዎችን አላስፈላጊ ምልልስ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አስችሏል።
አገልግሎቱ በዲጂታል ስታንዳርድ የሚመራ በመሆኑ፣ ተገልጋዮች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ንብረታቸውን እንዲቆጥቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታውን ይበልጥ ለማጠናከር በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና በሌሎች 15 ከተማ አስተዳደሮች የማዕከሉን ግንባታ ለማስፋፋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ አስራት ገልጸዋል።
በተጨማሪም በፍትህ፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማካተት አዳዲስ ሶፍትዌሮችን የማበልጸግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በማዕከሉ አገልግሎት ሲያገኙ ያነጋገርናቸው ባለጉዳዮች በበኩላቸው፣ አሰራሩ ዘመናዊ መሆኑንና ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ጉዳዮቻቸውን በአንድ ቦታ መጨረስ መቻላቸው ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል። “ቀደም ሲል ለቀናት የምንመላለስባቸውን ጉዳዮች አሁን በአጭር ሰዓታት ውስጥ መጨረስ ችለናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
