የካፈቾ ብሔር የዘመን መለወጫ (የቤኔ ሻዴዬ ባሮ) በቦንጌ ሻንበቶ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።

Spread the love

የካፈቾ ብሔር የጥንት ታሪክና የዳበረ ባህል ባለቤት ነው።

ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ለዚህ ትውልድ የደረሱ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች አሏቸው።

ከነዚህም አንዱ ዛሬ በደማቅ ሁኔታ በቦንጌ ሻንበቶ እየተከበረ ያለው የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ “የቤኔ ሻዴዬ ባሮ”በዓል ነው።

የቤኔ ሻዴዬ ባሮ በካፈቾዎች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የብሔሩ ታላቅ ዕሴትና የማይዳሰስ ቅርስ ነው።

የካፋ ህዝብ ዘመን አቆጣጠር የአዝመራ ወቅትን መሠረት አድርጎ የሚከናወን ሲሆን
በዚህ አቆጣጠሩም ልክ ለበዓሉ 77 ቀናት ሲቀሩት በቁጥሩ መሠረት ልዩ ስያሜ እየሰጠ የሰባ ሰባት አዝመራ፣ የሰባ አዝመራ፣የስልሳ አዝመራ እያተባለ 25 ቀናት ሲቀሩት ሞፈር ቀንበሩን እንደሚያሳርፍ ይነገራል። በዚህም አርሶ አደሩ በሬውን ያሳርፋል፤ አሮጌው አመት በአዲስ ሲተካ የክረምቱ ጭጋጊ አልፎ ፀዳይ ስገባ ካፈቾዎች ቦንጌ ሻንበቶ ላይ በመገኘት በዓላቸውን ከንጉሱ ዘንድ ቀርበው በጋራ ያከብራሉ።

በዚህ ህዝባዊ በዓል ንጉሱ የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም የሚገመግሙበትና የተሻለ የፈፀመን ለበለጠ ስልጣን የሚያጩበት፣ በአፈፃፀሙ ወደ ኋላ የቀረን ከስልጣን የሚያወርዱበት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው በዓል ነው።

ይህም የጥንት የካፈቾ ነገስታት ማህበራዊና አስተዳደራዊ ችግሮችን በሠላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ የሚፈቱበት ዛሬም ድረስ ይዘውት የቀጠሉት ታላቅ ዕሴት ነው።

በዘንድሮ በዓል ላይ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ከክልሉ ሁሉም ዞኖች እንግዶች የተጋበዙ ሲሆን ይህም የበዓሉን የወል እውነት በማጽናት ለሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል።

ይህን ድንቅ የብሔሩ መገለጫ የሆነውን ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት እንዲሆንና የቱሪዝም ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ ማክበር እንደሚጠበቅ ነው ያነጋገርናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች የገለጹት፡፡

በበዓሉ ከአከባቢው ተወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች በተጨማሪ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እየተደሙ ይገኛሉ።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *