ኮሌጁ የህበረሰብ ችግር ሊፈቱ በሚችሉ የስራ ዘርፎች ላይ ባለሙያዎችን በማደራጀት የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገለጸ።

Spread the love

የታርጫ ፖሊ ቴክንክ ኮሌጅ ላለፉት በርካታ አመታት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ስራ ፈጣሪ ዜጎች እንዲበራከቱ እየሰራ ይገኛል።

የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ኤፍሬም አይሳ ኮሌጁ አሁን ላይ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ በኮሌጁ የሚሰጠውን ስልጠና ያጠናቀቁ ባለሙያዎችን የአከባቢውን ማህበረሰብ ችግር በሚፈቱ ዘርፎች በማደራጀት የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኮሌጁ ከተደራጁ አራት ማህበራት ሁለቱ ወደ ተግባር ገብተው በተለይ በአከባቢው አዲስ የሆነውን የቴራዞ እና የብሎኬት ምርት እየተመረተ እንደሚገኝም ተገልጧል።

በእነዚህ ማህበራት ተደራጅተው በኮሌጁ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ 26 ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም አቶ ኤፍሬም አንስተዋል።

በተለይ የቴራዞ ምርት በአከባቢው ስመረት የመጀመሪያ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም የማህበሩ ምርቶች ለኮሪደር ልማት ስራዎችና ለአከባቢው አገለግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረም አስረድተዋል።

መንግስት የመነሻ ካፕታል ብድር ማመቻቸቱን የሚገልፀው የTTZ የግንባታ ግብአቶች ማምረቻ ማህበር አስተባባሪ ኢንስትራክተር ተባረክ ታምራት ምርቱን በጥራት በማምረት ለማህበረሰቡ እየቀረቡ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ከዚህ በፊት የኮሌጁ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰልጣኝ እንደሆነ የገለፀው ወጣት ጥላሁን ሀይሌ በበኩሉ መንግስት ባመቻቸው የስራ እድል በመደራጀት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

ወጣት እንቁ በቀለ የጎጆ ብሎኬት ማምረቻ ማህበር ሰብሳቢ ሲሆን የብሎኬት ምርት በአከባቢው ማምረት ምርቱን ከሌሎች አከባቢ በማስመጣት የሚወጣውን ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት እንደሚያስቀር አስረድቷል።

የኮሌጁ የቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሽግግር ዘርፍ ዲን ኢንስትራክተር ሀረገወይን ወርቁ በበኩላቸው በዘርፉ ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማምረት የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *