




በካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው 2ኛው የብልፅግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ የማጠቃለያ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በመድረኩ ለውይይት የሚሆን መነሻ ሰነድ የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ አቅርቧል።
አቶ አጥናፉ በሪፖርታቸው የብልጽግና ፓርቲ ጽንሰ ሀሣብና እሳቤ በአመራሩና አባላት ውስጥ በማስረጽ ፓርቲያችንን ለማጠናከር በርካታ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን አስታውሷል።
አቶ አጥናፉ አክሎ ብልጽና ፓርቲ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ለህዝብ የገባቸውን ቃሎች በተግባር እየፈፀመ ያለና በተጨባጭ ህዝቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እየለወጠ የሚገኝ ጠንካራ ፓርቲ ነው ብሏል።
ፓርቲው በሰራው ጠንካራ ሥራ በህዝቡ ውስጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር በርካታ ሰው ተኮር የልማትና የመሰረተ ልማት ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት የመንግስት ዋና ተጠሪው በቀጣይም ይህንኑ በጎ ሥራ ፓርቲው አጠናክሮ ያስቀጥላል በማለት ተናግሯል።
በኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና በመሰረተ ልማት መስኮች በዞኑ የተከናወኑ በርካታ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች የመኖራቸውን ያክል በተቃራኒው ደግሞ በቀጣይ ተለቅሞ መፈታት ያለባቸው ተግዳሮቶች በገጠርና ከተማ መኖራቸውን የመንግስት ዋና ተጠሪው አጽንኦት ሰጥቷል።
በኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሣብ አስተያየት ተነስቷል። እንደ ተሳታፊዎች አስተያየት በሀገር ደረጃ ፓርቲው ላለፉት ዓመታት በርካታ ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ መድረሱ ለችግሮች የማይበገርና ጽናት ያለው ፓርቲ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ፓርቲው በሁሉም መስኮች የጀመራቸውን ሥራዎች ህዝብን በማሳተፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የገለጹት ተሳታፊዎች በተለይ በከተማና ገጠር መሰረተ ልማት የተጎዱ አካባቢዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቷል።
ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አጥናፉ ኃይሌና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ዝርዝር ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
የተጓደሉ የኢንስፐክሽንና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ኮሚቴ አባላት ፕሮፖዛል ቀርቦ በኮንፈረንሱ ፀድቋል።
በመጨረሻም በሀገር ደረጃ በቀጣይ የሚካሄደውን 2ኛውን የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የሚሳተፉ አካላትን ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች መልምሎ በማጽደቅ ኮንፈረንሱ ተጠናቋል።
በኮንፈረንሱ የካፋ ዞን ማዕከል አጠቃላይ አመራሩን ጨምሮ የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንድሁም ከሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የተወከሉ አካላት ተሳትፏል ሲል የዘገበው የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
